← Numbers (16/36) → |
1. | የሌዊም ልጅ የቀዓት ልጅ የይስዓር ልጅ ቆሬ ከሮቤልም ልጆች የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን የፋሌትም ልጅ ኦን በሙሴ ላይ ተነሡ። ች የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን የፋሌትም ልጅ ኦን በሙሴ |
2. | ከእስራኤልም ልጆች ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች ከእነርሱ ጋር ወሰዱ፤ ከጉባኤው የተመረጡ ዝናቸውም የተሰማ የማኅበሩ አለቆች ነበሩ። |
3. | በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው። ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ? አሉ። |
4. | ሙሴም በሰማ ጊዜ በግምባሩ ወደቀ፤ |
5. | ለቆሬም ለወገኑም ሁሉ። ነገ እግዚአብሔር ለእርሱ የሚሆነውን፥ ቅዱስም የሚሆነውን ያስታውቃል፤ የመረጠውንም ሰው ወደ እርሱ ያቀርበዋል። |
6. | እንዲሁ አድርጉ፤ ቆሬና ወገንህ ሁሉ፥ ጥናዎቹን ውሰዱ፤ |
7. | ነገም በእግዚአብሔር ፊት እሳት አድርጉባቸው፥ ዕጣንም ጨምሩባቸው፤ እንዲህም ይሆናል፤ እግዚአብሔር የሚመርጠው እርሱ ቅዱስ ይሆናል፤ እናንተ የሌዊ ልጆች ሆይ እጅግ አብዝታችኋል ብሎ ተናገራቸው። |
8. | ሙሴም ቆሬን አለው። እናንተ የሌዊ ልጆች፥ ስሙ፤ |
9. | የእስራኤል አምላክ ከእስራኤል ማኅበር የለያችሁ፥ የእግዚአብሔርንም ማደሪያ አገልግሎት ትሠሩ ዘንድ፥ እንድታገለግሉአቸውም በማኅበሩ ፊት ትቆሙ ዘንድ ወደ እርሱ ያቀረባችሁ አይበቃችሁምን? |
10. | አንተን ከአንተም ጋር የሌዊን ልጆች ወንድሞችህን ሁሉ ወደ እርሱ አቅርቦአል፤ ክህነትንም ደግሞ ትፈልጋላችሁን? |
11. | ስለዚህም አንተና ወገንህ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ተሰብስባችኋል፤ በእርሱም ላይ ታጕረመርሙ ዘንድ አሮን ማን ነው? |
12. | ሙሴም የኤልያብን ልጆች ዳታንና አቤሮንን እንዲጠሩአቸው ላከ፤ እነርሱም። አንመጣም፤ |
13. | በምድረ በዳ ትገድለን ዘንድ ወተትና ማር ከምታፈስሰው ምድር ያወጣኸን አይበቃህምን? ደግመህ በእኛ ላይ ራስህን አለቃ ታደርጋለህን? |
14. | ደግሞ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር አላገባኸንም፥ እርሻና ወይንም አላወረስኸንም፤ የእነዚህንስ ሰዎች ዓይኖቻቸውን ታወጣለህን? አንመጣም አሉ። |
15. | ሙሴም እጅግ ተቈጣ፥ እግዚአብሔርንም። ወደ ቍርባናቸው አትመልከት፤ እኔ ከእነርሱ አንድ አህያ ስንኳ አልወሰድሁም፥ ከእነርሱም አንድ ሰው አልበደልሁም አለው። |
16. | ሙሴም ቆሬን። ነገ አንተ፥ ወገንህም ሁሉ፥ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁኑ፤ |
17. | ሁላችሁም ጥናዎቻችሁን ውሰዱ፥ ዕጣንም አድርጉባቸው፥ እያንዳንዳችሁም ጥናዎቻችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት አምጡ፥ ሁለት መቶ አምሳ ጥናዎች፤ አንተ ደግሞ አሮንም ጥናዎቻችሁን አምጡ አለው። |
18. | እያንዳንዱም ጥናውን ወሰደ፥ እሳትም አደረገበት፥ ዕጣንም ጨመረበት፥ ከሙሴና ከአሮንም ጋር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆመ። |
19. | ቆሬም ማኅበሩን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእነርሱ ላይ ሰበሰበ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለማኅበሩ ሁሉ ተገለጠ። |
20. | እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። |
21. | ሁሉን በቅጽበት አጠፋቸው ዘንድ ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ። |
22. | እነርሱም በግምባራቸው ወድቀው። አምላክ ሆይ፥ አንተ የሰው ሁሉ ነፍስ አምላክ፥ አንድ ሰው ኃጢአት ቢሠራ አንተ በማኅበሩ ሁሉ ላይ ትቈጣለህን? አሉ። |
23. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
24. | ለማኅበሩ። ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ዙሪያ ፈቀቅ በሉ ብለህ ንገራቸው። |
25. | ሙሴም ተነሥቶ ወደ ዳታንና ወደ አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት። |
26. | ማኅበሩንም። እባካችሁ፥ ከእነዚህ ክፉዎች ድንኳን ፈቀቅ በሉ፤ በኃጢአታቸውም ሁሉ እንዳትጠፉ ለእነርሱ የሆነውን ሁሉ አትንኩ ብሎ ተናገራቸው። |
27. | ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ከዙሪያውም ሁሉ ፈቀቅ አሉ፤ ዳታንና አቤሮንም ሴቶቻቸውም ልጆቻቸውም ሕፃናቶቻቸውም ወጥተው በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ቆሙ። |
28. | ሙሴም አለ። ይህን ሥራ ሁሉ አደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ላከኝ እንጂ ከልቤ እንዳይደለ በዚህ ታውቃላችሁ። |
29. | እነዚህ ሰዎች ሰው እንደሚሞት ቢሞቱ፥ ወይም እንደ ሰው ሁሉ ቢቀሠፉ እግዚአብሔር አልላከኝም። |
30. | እግዚአብሔር ግን አዲስ ነገር ቢፈጥር፥ ምድርም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ለእነርሱም ያለውን ሁሉ ብትውጣቸው፥ በሕይወታቸውም ወደ ሲኦል ቢወርዱ፥ ያን ጊዜ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን እንደ ናቁ ታውቃላችሁ። |
31. | እንዲህም ሆነ፤ ይህን ቃል ሁሉ መናገር በፈጸመ ጊዜ ከበታቻቸው ያለው መሬት ተሰነጠቀ፤ |
32. | ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ቤተ ሰቦቻቸውንም፥ ለቆሬም የነበሩትን ሰዎች ሁሉ፥ ዕቃዎቻቸውንም ሁሉ ዋጠቻቸው። |
33. | እነርሱም ለእነርሱም የነበሩ ሁሉ በሕይወታቸው ወደ ሲኦል ወረዱ፤ ምድሪቱም ተዘጋችባቸው፥ ከጉባኤውም መካከል ጠፉ። |
34. | በዙሪያቸው የነበሩ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ከጩኸታቸው የተነሣ። ምድሪቱ እንዳትውጠን ብለው በረሩ። |
35. | እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥታ ያጥኑ የነበሩትን ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች በላች። |
36. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
37. | ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር እንዲህ ብለህ ንገረው። ተቀድሰዋልና ጥናዎቹን ከተቃጠሉት ዘንድ ውሰድ፥ እሳቱንም ወደ ውጭ ጣለው፤ |
38. | በኃጢአታቸው ሰውነታቸውን ያጠፉትን የእነዚያን ሰዎች ጥናዎች ጠፍጥፈህ ለመሠዊያ መለበጫ አድርጋቸው፤ በእግዚአብሔር ፊት አቅርበዋቸዋልና የተቀደሱ ናቸው፥ ለእስራኤልም ልጆች ምልክት ይሆናሉ። |
39. | ካህኑም አልዓዛር የተቃጠሉት ሰዎች ያቀረቡአቸውን የናስ ጥናዎች ወስዶ ጠፍጥፎም ለመሠዊያው መለበጫ አደረጋቸው። |
40. | በቆሬና በወገኑ የደረሰው እንዳይደርስበት፥ ከአሮን ልጆች ያልሆነ ሌላ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ዕጣን ያጥን ዘንድ እንዳይቀርብ፥ እግዚአብሔር በሙሴ እንደ ተናገረው፥ ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ አደረጋቸው። |
41. | በነጋውም የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ። እናንተ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ገድላችኋል ብለው በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ። |
42. | እንዲህም ሆነ፤ ማኅበሩ በሙሴና በአሮን ላይ በተሰበሰቡ ጊዜ ወደ መገናኛው ድንኳን አዩ፤ እነሆም፥ ደመናው ሸፈነው፥ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠ። |
43. | ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት መጡ። |
44. | እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
45. | ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ፥ እኔም በቅጽበት አጠፋቸዋለሁ። በግምባራቸውም ወደቁ። |
46. | ሙሴም አሮንን። ጥናህን ውሰድ፥ ከመሠዊያውም ላይ እሳት አድርግበት፥ ዕጣንም ጨምርበት፥ ወደ ማኅበሩም ፈጥነህ ውሰደው አስተስርይላቸውም፤ ከእግዚአብሔር ፊት ቍጣ ወጥቶአልና መቅሠፍት ጀምሮአል አለው። |
47. | አሮንም ሙሴ እንደ ተናገረው ጥናውን ወስዶ ወደ ጉባኤው መካከል ሮጠ፤ እነሆም፥ መቅሠፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር፤ ዕጣንም ጨመረ፥ ለሕዝቡም አስተሰረየላቸው። |
48. | በሙታንና በሕያዋን መካከል ቆመ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ። |
49. | በቆሬም ምክንያት ከሞቱት ሌላ በመቅሠፍቱ የሞቱት አሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። |
50. | አሮንም ወደ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተመለሰ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ። |
← Numbers (16/36) → |