Numbers (14/36)  

1. ማኅበሩም ሁሉ ድምፃቸውን አንሥተው ጮኹ፤ ሕዝቡም በዚያ ሌሊት አለቀሱ።
2. የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ። በግብፅ ምድር ሳለን ምነው በሞትን ኖሮ! ወይም በዚህ ምድረ በዳ ምነው በሞትን ኖሮ!
3. እግዚአብሔርም በሰይፍ እንሞት ዘንድ ወደዚች ምድር ለምን ያገባናል? ሴቶቻችንና ልጆቻችን ምርኮ ይሆናሉ፤ ወደ ግብፅ መመለስ አይሻለንምን? አሉአቸው።
4. እርስ በርሳቸውም። ኑ፥ አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ ተባባሉ።
5. ሙሴና አሮንም በእስራኤል ልጆች ጉባኤ ፊት በግምባራቸው ወደቁ።
6. ምድርን ከሰለሉት ጋር የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤
7. ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ። ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም ናት።
8. እግዚአብሔርስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርስዋንም ይሰጠናል።
9. ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአል፥ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው ብለው ተናገሩአቸው።
10. ማኅበሩ ሁሉ ግን በድንጋይ ይወግሩአቸው ዘንድ ተማከሩ። የእግዚአብሔርም ክብር ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ተገለጠ።
11. እግዚአብሔርም ሙሴን። ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? በፊቱስ ባደረግሁት ተአምራት ሁሉ እስከ መቼ አያምንብኝም?
12. ከርስታቸው አጠፋቸው ዘንድ በቸነፈር እመታቸዋለሁ፤ አንተም ከእነርሱ ለሚበዛና ለሚጠነክር ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው።
13. ሙሴም እግዚአብሔርን አለው። ግብፃውያን ይሰማሉ፤ ይህን ሕዝብ ከመካከላቸው በኃይልህ አውጥተኸዋልና፤
14. ለዚችም ምድር ሰዎች ይናገራሉ። አንተ እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ መካከል እንደ ሆንህ ሰምተዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ ፊት ለፊት ተገልጠሃል፥ ደመናህም በላያቸው ቆሞአል፥ በቀንም በደመና ዓምድ፥ በሌሊትም በእሳት ዓምድ በፊታቸው ትሄዳለህ።
15. ይህን ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ብትገድል ዝናህን የሰሙ አሕዛብ።
16. እግዚአብሔር ይህን ሕዝብ ወደ ማለላቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና በምድረ በዳ ገደላቸው ብለው ይናገራሉ።
18. አሁንም፥ እባክህ። እግዚአብሔር ታጋሽና ምሕረቱ የበዛ፥ አበሳንና መተላለፍን ይቅር የሚል፥ ኃጢአተኞችንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን ኃጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ በልጆች ላይ የሚያመጣ ነው ብለህ እንደ ተናገርህ፥ የጌታ ኃይል ታላቅ ይሁን።
19. ይህን ሕዝብ ከግብፅ ምድር ካወጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው፥ እባክህ፥ እንደ ምሕረትህ ብዛት የዚህን ሕዝብ ኃጢአት ይቅር በል።
20. እግዚአብሔርም አለ። እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ፤
21. ነገር ግን እኔ ሕያው ነኛ በእውነት የእግዚአብሔር ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል።
22. በግብፅ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ተአምራቴንና ክብሬን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ አሥር ጊዜ ስለ ተፈታተኑኝ፥
23. ነገሬንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ከእነርሱም የናቀኝ ሰው ሁሉ አያያትም፤
24. ባሪያዬ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ ፈጽሞም ስለተከተለኝ እርሱ ወደ ገባባት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል።
25. አማሌቅና ከነዓናዊውም በሸለቆው ውስጥ ተቀምጦአል፤ በነጋው ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ።
26. እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
27. የሚያጕረመርምብኝን ይህን ክፉ ሕዝብ እስከ መቼ እታገሠዋለሁ? በእኔ ላይ የሚያጕረመርሙትን የእስራኤልን ልጆች ማጕረምረም ሰማሁ።
28. እንዲህ በላቸው። እኔ ሕያው ነኝና በጆሮዬ እንደ ተናገራችሁት እንዲሁ በእውነት አደርግባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤
29. በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ፤ የተቆጠራችሁ ሁሉ፥ እንደቁጥራችሁ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የሆነ ሁሉ፥ እናንተ ያጕረመረማችሁብኝ፥
30. ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር በእርስዋ አስቀምጣችሁ ዘንድ እጄን ዘርግቼ ወደ ማልሁላችሁ ምድር በእውነት እናንተ አትገቡም።
31. ምርኮኛ ይሆናሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን እነርሱን አገባቸዋለሁ፥ እናንተም የናቃችኋትን ምድር ያውቃሉ።
32. እናንተ ግን በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ።
33. ልጆቻችሁም በምድረ በዳ አርባ ዓመት ይቅበዘበዛሉ፥ በድኖቻችሁም በምድረ በዳ እስኪጠፉ ድረስ ግልሙትናችሁን ይሸከማሉ።
34. ምድሪቱን በሰላለችሁባት ቀን ቍጥር፥ አርባ ቀን፥ ስለ አንድ ቀንም አንድ ዓመት፥ ኃጢአታችሁን አርባ ዓመት ትሸከማላችሁ፥ ቍጣዬንም ታውቃላችሁ።
35. እኔ እግዚአብሔር። በእኔ ላይ በተሰበሰበ በዚህ ክፉ ማኅበር ሁሉ ላይ እንዲህ አደርጋለሁ ብዬ ተናገርሁ፤ በዚህ ምድረ በዳ ያልቃሉ፥ በዚያም ይሞታሉ።
36. ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሙሴ ልኮአቸው የተመለሱት ሰዎች ክፉ ወሬም ስለ ምድሪቱ እያወሩ በእርሱ ላይ ማኅበሩ ሁሉ እንዲያጕረመርሙ ያደረጉ፥
37. ክፉ ወሬ ያወሩ እነዚያ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት በመቅሠፍት ሞቱ።
38. ነገር ግን ምድሪቱን ሊሰልሉ ከሄዱ ሰዎች የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ በሕይወት ተቀመጡ።
39. ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ነገረ፥ ሕዝቡም እጅግ አዘኑ።
40. በነጋውም ማልደው ተነሡ፥ ወደ ተራራውም ራስ መጥተው። እነሆ፥ መጣን፤ እኛ በድለናልና እግዚአብሔር ወዳለው ስፍራ እንወጣለን አሉ።
41. ሙሴም አለ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይጠቅማችሁም።
42. እግዚአብሔር በእናንተ መካከል አይደለምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ።
43. አማሌቃዊና ከነዓናዊ በፊታችሁ ናቸውና በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ እግዚአብሔርን ከመከተል ተመልሳችኋልና እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይሆንም።
44. እነርሱ ግን ወደ ተራራው ራስ ሊወጡ ደፈሩ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦትና ሙሴ ከሰፈሩ አልተነሡም።
45. በዚያም ተራራ ላይ የተቀመጡ አማሌቃዊና ከነዓናዊ ወረዱ፥ መትተዋቸውም እስከ ሔርማ ድረስ አሳደዱአቸው።

  Numbers (14/36)