← Numbers (13/36) → |
1. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
2. | ለእስራኤል ልጆች የምሰጣትን የከንዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ሰዎችን ላክ፤ ከአባቶች ነገድ ሁሉ እያንዳንዱ በመካከላቸው አለቃ የሆነ አንድ ሰው ትልካላችሁ። |
3. | ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከፋራን ምድረ በዳ ላካቸው፤ እነርሱም ሁሉ የእስራኤል ልጆች አለቆች ነበሩ። |
4. | ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ከሮቤል ነገድ የዘኩር ልጅ ሰሙኤል፤ |
5. | ከስምዖን ነገድ የሱሬ ልጅ ሰፈጥ፤ |
6. | ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፤ |
7. | ከይሳኮር ነገድ የዮሴፍ ልጅ ይግአል፤ |
8. | ከኤፍሬም ነገድ የነዌ ልጅ አውሴ፤ |
10. | ከብንያም ነገድ የራፉ ልጅ ፈልጢ፤ ከዛብሎን ነገድ የሰዲ ልጅ ጉዲኤል፤ |
11. | ከዮሴፍ ነገድ እርሱም የምናሴ ነገድ የሱሲ ልጅ ጋዲ፤ |
12. | ከዳን ነገድ የገማሊ ልጅ ዓሚኤል፤ |
13. | ከአሴር ነገድ የሚካኤል ልጅ ሰቱር፤ |
14. | ከንፍታሌም ነገድ የያቢ ልጅ ናቢ፤ |
15. | ከጋድ ነገድ የማኪ ልጅ ጉዲኤል። |
16. | ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ሙሴ የላካቸው ሰዎች ስም ይህ ነው። ሙሴም የነዌን ልጅ አውሴን ኢያሱ ብሎ ጠራው። |
17. | ሙሴም የከነዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ላካቸው፥ አላቸውም። ከዚህ በደቡብ በኩል ውጡ፥ ወደ ተራሮችም ሂዱ፤ |
18. | ምድሪቱንም እንዴት እንደ ሆነች፥ በእርስዋም የሚኖሩ ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፥ |
19. | ጥቂቶች ወይም ብዙዎች እንደ ሆኑ፥ የሚኖሩባትም ምድር መልካም ወይም ክፉ፥ የሚኖሩባቸውም ከተሞች ሰፈሮች ወይም አምቦች እንደ ሆኑ፥ |
20. | ምድሪቱም ወፍራም ወይም ስስ ዛፍ ያለባት ወይም የሌለባት እንደ ሆነች እዩ፤ ከምድሪቱ ፍሬ አምጡ፤ አይዞአችሁ። በዚያን ጊዜም ወይኑ አስቀድሞ ፍሬ የሚያፈራበት ወራት ነበረ። |
21. | ወጡም ምድሪቱንም ከጺን ምድረ በዳ በሐማት ዳር እስካለችው እስከ ረአብ ድረስ ሰለሉ። |
22. | በደቡብም በኩል ውጡ፥ ወደ ኬብሮንም ደረሱ፤ በዚያም የዔናቅ ልጆች አኪመን፥ ሴሲ፥ ተላሚ ነበሩ። ኬብሮንም በግብፅ ካለችው ከጣኔዎስ በፊት ሰባት ዓመት ተሠርታ ነበር። |
23. | ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጡ፥ ከዚያም ከወይኑ አንድ ዘለላ የነበረበትን አረግ ቈረጡ፥ ሁለቱም ሰዎች በመሎጊያ ተሸከሙት፤ ደግሞም ከሮማኑ ከበለሱም አመጡ። |
24. | የእስራኤል ልጆች ከዚያ ስለ ቈረጡት ዘለላ የዚያን ስፍራ ስም የኤሽኮል ሸለቆ ብለው ጠሩት። |
25. | ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ። |
26. | በፋራን ምድረ በዳና በቃዴስ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሄደው ደረሱ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፥ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው። |
27. | እንዲህም ብለው ነገሩት። ወደ ላክኸን ምድር ደረስን፥ እርስዋም ወተትና ማር ታፈስሳለች፥ ፍሬዋም ይህ ነው። |
28. | ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኃያላን ናቸው። ከተሞቻቸውም የተመሸጉ እጅግም የጸኑ ናቸው፤ ደግሞም በዚያ የዔናቅን ልጆች አየን። |
29. | በደቡብም ምድር አማሌቅ ተቀምጦአል፤ በተራሮቹም ኬጢያዊና ኢያቡሳዊ አሞራዊም ተቀምጠዋል፤ ከነዓናዊም በባሕር ዳርና በዮርዳኖስ አጠገብ ተቀምጦአል። |
30. | ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና። ማሸነፍ እንችላለንንና እንውጣ፥ እንውረሰው አለ። |
31. | ከእርሱ ጋር የወጡ ሰዎች ግን። በኃይል ከእኛ ይበረታሉና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም አሉ። |
32. | ስለ ሰለሉአትም ምድር ክፉ ወሬ ለእስራኤል ልጆች እያወሩ። እኛ ዞረን የሰለልናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ምድር ናት፤ በእርስዋም ዘንድ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ረጃጅም ሰዎች ናቸው። |
33. | በዚያም ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን ኔፊሊም፥ የዔናቅን ልጆች፥ አየን፤ እኛም በዓይናችን ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን፥ ደግሞም እኛ በዓይናቸው ዘንድ እንዲሁ ነበርን አሉ። |
← Numbers (13/36) → |