| ← Numbers (10/36) → |
| 1. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 2. | ሁለት የብር መለከቶች አጠፍጥፈህ ለአንተ አድርግ፤ ማኅበሩን ለመጥራት ከሰፈራቸውም ለማስጓዝ ይሁኑልህ። |
| 3. | ሁለቱም መለከቶች በተነፉ ጊዜ ማኅበሩ ሁሉ ወደ አንተ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይሰብሰቡ። |
| 4. | አንድ መለከት ሲነፋ ታላላቆቹ የእስራኤል አእላፍ አለቆች ወደ አንተ ይሰብሰቡ። |
| 5. | መለከትንም ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በምሥራቅ በኩል የሰፈሩት ይጓዙ። |
| 6. | ሁለተኛውንም ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በደቡብ በኩል የሰፈሩት ይጓዙ፤ ለማስጓዝ መለከትን ይነፋሉ። |
| 7. | ጉባኤውም በሚሰበሰብበት ጊዜ ንፉ፥ ነገር ግን ድምፁን ከፍ አታድርጉት። |
| 8. | የአሮንም ልጆች ካህናቱ መለከቶቹን ይንፉ፤ እነርሱም ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ይሁኑ። |
| 9. | በሚገፋችሁም ጠላት ላይ በምድራችሁ ወደ ሰልፍ ስትወጡ ከፍ ባለ ድምፅ መለከቶቹን ንፉ፤ በእግዚአብሔርም በአምላካችሁ ፊት ትታሰባላችሁ፥ ከጠላቶቻችሁም ትድናላችሁ። |
| 10. | ደግሞ በደስታችሁ ቀን፥ በበዓላታችሁም ዘመን፥ በወርም መባቻ፥ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በደኅንነት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቶቹን ንፉ፤ እነርሱም በአምላካችሁ ፊት ለመታሰቢያ ይሆኑላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። |
| 11. | በሁለተኛውም ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያኛው ቀን እንዲህ ሆነ፤ ደመናው ከምስክሩ ማደሪያ ላይ ተነሣ። |
| 12. | የእስራኤልም ልጆች ከሲና ምድረ በዳ በየጕዞአቸው ተጓዙ፤ ደመናውም በፋራን ምድረ በዳ ቆመ። |
| 13. | በመጀመሪያም እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ ተጓዙ። |
| 14. | በመጀመሪያም የይሁዳ ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን አለቃ ነበረ። |
| 15. | በይሳኮርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሶገር ልጅ ናትናኤል አለቃ ነበረ። |
| 16. | በዛብሎንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኬሎን ልጅ ኤልያብ አለቃ ነበረ። |
| 17. | ማደሪያውም ተነቀለ፤ ማደሪያውንም የተሸከሙ የጌድሶን ልጆችና የሜራሪ ልጆች ተጓዙ። |
| 18. | የሮቤልም ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር አለቃ ነበረ። |
| 19. | በስምዖንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል አለቃ ነበረ። |
| 20. | በጋድም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ አለቃ ነበረ። |
| 21. | ቀዓታውያንም መቅደሱን ተሸክመው ተጓዙ፤ እነዚህም እስኪመጡ ድረስ እነዚያ ማደሪያውን ተከሉ። |
| 22. | የኤፍሬምም ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ አለቃ ነበረ። |
| 23. | በምናሴም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል አለቃ ነበረ። |
| 24. | በብንያምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን አለቃ ነበረ። |
| 25. | ከሰፈሮቹ ሁሉ በኋላ የሆነ የዳን ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር አለቃ ነበረ። |
| 26. | በአሴርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኤክራን ልጅ ፋግኤል አለቃ ነበረ። |
| 27. | በንፍታሌምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የዔናን ልጅ አኪሬ አለቃ ነበረ። |
| 28. | እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ጕዞ በየሠራዊታቸው ነበረ፤ እነርሱም ተጓዙ። |
| 29. | ሙሴም የሚስቱን አባት የምድያማዊውን የራጉኤልን ልጅ ኦባብን። እግዚአብሔር። ለእናንተ እሰጠዋለሁ ወዳለው ስፍራ እንሄዳለን፤ እግዚአብሔር ስለ እስራኤል መልካምን ነገር ተናግሮአልና አንተ ከእኛ ጋር ና፥ መልካምን እናደርግልሃለን አለው። |
| 30. | እርሱም። አልሄድም፥ ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ዘመዶቼ እሄዳለሁ አለው። |
| 31. | እርሱም። እባክህ፥ በምድረ በዳ የምንሰፍርበትን አንተ ታውቃለህና፥ እንደ ዓይኖቻችንም ትሆንልናለህና አትተወን፤ |
| 32. | ከእኛም ጋር ብትሄድ እግዚአብሔር ከሚያደርግልን መልካም ነገር ሁሉ እኛ ለአንተ እናደርጋለን አለ። |
| 33. | ከእግዚአብሔርም ተራራ የሦስት ቀን መንገድ ያህል ተጓዙ፤ የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት የሚያድርበትን ስፍራ ይፈልግላቸው ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ ቀደማቸው። |
| 34. | ከሰፈራቸውም በተጓዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ደመና ቀን ቀን በላያቸው ነበረ። |
| 35. | ሙሴም ታቦቱ በተጓዘ ጊዜ። አቤቱ፥ ተነሣ፥ ጠላቶችህም ይበተኑ፥ የሚጠሉህም ከፊትህ ይሽሹ ይል ነበር። |
| 36. | ባረፈም ጊዜ። አቤቱ፥ ወደ እስራኤል እልፍ አእላፋት ተመለስ ይል ነበር። |
| ← Numbers (10/36) → |