| Numbers (1/36) → |
| 1. | እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን፥ ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ዓመት እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 2. | የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ ድምር፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ በየስማቸው ቍጥር፥ ወንዱን በየራሱ፥ ውሰዱ። |
| 3. | ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን፥ ከእስራኤል ወደ ሰልፍ የሚወጡትን ሁሉ፥ አንተና አሮን በየሠራዊቶቻቸው ቍጠሩአቸው። |
| 4. | ከየነገዱም አንድ ሰው የአባቶቹ ቤት አለቃ ከእናንተ ጋር ይሁን። |
| 5. | ከእናንተም ጋር የሚቆሙት ሰዎች ስሞቻቸው እነዚህ ናቸው፤ ከሮቤል የሰዲዮር ልጅ |
| 6. | ኤሊሱር፥ ከስምዖን የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፥ |
| 7. | ከይሁዳ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፥ |
| 8. | ከይሳኮር የሶገር ልጅ ናትናኤል፥ |
| 10. | ከዛብሎን የኬሎን ልጅ ኤልያብ፥ ከዮሴፍ ልጆች ከኤፍሬም የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፥ ከምናሴ የፍዳሱ ልጅ ገማልኤል፥ |
| 12. | ከብንያም የጋዴዮን ልጅ አቢዳን፥ ከዳን የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፥ |
| 13. | ከአሴር የኤክራን ልጅ ፋግኤል፥ |
| 14. | ከጋድ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ፥ |
| 15. | ከንፍታሌም የዔናን ልጅ አኪሬ። |
| 16. | ከማኅበሩ የተመረጡ የእስራኤል አእላፍ ታላላቆች፥ የአባቶቻቸው ነገድ አለቆች እነዚህ ናቸው። |
| 17. | ሙሴና አሮንም እነዚህን በስማቸው የተጠሩትን ሰዎች ወሰዱአቸው፤ |
| 18. | በሁለተኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ማኅበሩን ሁሉ ሰበሰቡአቸው፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን በየራሱ በየወገኑም በየአባቶቻቸውም ቤቶች በየስማቸው ቍጥር ትውልዳቸውን ተናገሩ። |
| 19. | እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በሲና ምድረ በዳ ቈጠራቸው። |
| 20. | የእስራኤል በኵር የሮቤል ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ |
| 21. | ከሮቤል ነገድ የተቈጠሩ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። |
| 22. | የስምዖን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች የተቈጠሩ፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ |
| 23. | ከስምዖን ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ። |
| 24. | የጋድ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ |
| 25. | ከጋድ ነገድ የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ አምሳ ነበሩ። |
| 26. | የይሁዳ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ |
| 27. | ከይሁዳ ነገድ የተቈጠሩት ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። |
| 28. | የይሳኮር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ |
| 29. | ከይሳኮር ነገድ የተቈጠሩት አምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። |
| 30. | የዛብሎን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ |
| 31. | ከዛብሎን ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። |
| 32. | ከዮሴፍ ልጆች፥ የኤፍሬም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ |
| 33. | ከኤፍሬም ነገድ የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። |
| 34. | የምናሴ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ |
| 35. | ከምናሴ ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። |
| 36. | የብንያም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ |
| 37. | ከብንያም ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። |
| 38. | የዳን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ |
| 39. | ከዳን ነገድ የተቈጠሩት ስድሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። |
| 40. | የአሴር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ |
| 41. | ከአሴር ነገድ የተቈጠሩት አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። |
| 42. | የንፍታሌም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ |
| 43. | ከንፍታሌም ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። |
| 44. | የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን አሥራ ሁለቱም የእስራኤል አለቆች የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው፤ እያንዳንዱ የአባቶቹ ቤት አለቃ ነበረ። |
| 45. | ከእስራኤልም ልጆች የተቈጠሩት ሁሉ፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ |
| 46. | የተቈጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ነበሩ። |
| 47. | ሌዋውያን ግን በየአባቶቻቸው ነገድ ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም። |
| 48. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። የሌዊን ነገድ አትቍጠረው፥ |
| 49. | ቍጥራቸውንም ከእስራኤል ልጆች ጋር አታድርግ፤ |
| 50. | ነገር ግን በምስክሩ ማደሪያና በዕቃዎች ሁሉ ለእርሱም በሚሆነው ነገር ሁሉ ላይ ሌዋውያንን አቁማቸው። ማደሪያውንና ዕቃዎችን ሁሉ ይሸከሙ፥ ያገልግሉትም፥ በማደሪያውም ዙሪያ ይስፈሩ። |
| 51. | ማደሪያውም ሲነሣ ሌዋውያን ይንቀሉት፤ ማደሪያውም በሰፈረ ጊዜ ሌዋውያን ይትከሉት፤ ሌላ ሰው ግን ቢቀርብ ይገደል። |
| 52. | የእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ በየሰፈሩ፥ በየዓላማውም፥ በየጭፍራውም ይሰፍራሉ። |
| 53. | ነገር ግን በእስራኤል ልጆች ላይ ቍጣ እንዳይወርድ ሌዋውያን በምስክሩ ማደሪያ ዙሪያ ይስፈሩ፤ ሌዋውያንም የምስክሩን ማደሪያ ይጠብቁ። |
| 54. | የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረጉ። |
| Numbers (1/36) → |