Nehemiah (6/13)  

1. እንዲህም ሆነ፤ ቅጥሩን እንደ ሠራሁ፥ ከፍራሹም አንዳች እንዳልቀረበት ሰንባላጥና ጦብያ ዓረባዊውም ጌሳም የቀሩትም ጠላቶቻችን ሰሙ፤ ነገር ግን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በበሮቹ ውስጥ ሳንቃዎቹን አላቆምሁም ነበር።
2. ሰንባላጥና ጌሳም። መጥተህ በኦኖ ቈላ ውስጥ ባሉት መንደሮች እንገናኝ ብለው ላኩብኝ፤ ነገር ግን ክፉ ያደርጉብኝ ዘንድ ያስቡ ነበር።
3. እኔም። ትልቅ ሥራ እሠራለሁ፥ እወርድም ዘንድ አይቻለኝም፤ ሥራውን ትቼ ወደ እናንተ በመውረዴ ስለ ምን ሥራው ይታጐላል? ብዬ መልእክተኞችን ላክሁባቸው።
4. እንዲህም ቃል አራት ጊዜ ላኩብኝ፤ እኔም እንደ ፊተኛው ቃል መለስሁላቸው።
5. ሰንባላጥም እንደ ፊተኛው ጊዜ ብላቴናውን አምስተኛ ጊዜ ላከብኝ፤
6. በእጁም ውስጥ። አንተና አይሁድ ዓመፅ እንድታስቡ፥ ስለዚህም ቅጥሩን እንድትሠራ፥ ንጉሣቸውም ትሆን ዘንድ እንድትወድድ በአሕዛብ ዘንድ ተሰምቶአል።
7. ደግሞም። ንጉሥ በይሁዳ አለ ብለው ስለ አንተ በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ ነቢያትን አቁመሃል፤ አሁንም ለንጉሡ ይህን ቃል ያወሩለታል፤ እንግዲህ መጥተህ በአንድነት እንማከር የሚል ክፍት ደብዳቤ ነበረ።
8. እኔም። አንተ ከልብህ ፈጥረኸዋል እንጂ እንደ ተናገርኸው ነገር ምንም የለም ብዬ ላክሁበት።
9. እነርሱም ሁሉ ሥራው እንዳይፈጸም። እጃቸው ይደክማል ብለው ያስፈራሩን ዘንድ ወደዱ፤ አሁንም፥ አምላክ ሆይ፥ እጄን አበርታ።
10. እኔም ወደ መሔጣብኤል ልጅ ወደ ድላያ ልጅ ወደ ሸማያ ቤት ገባሁ፤ እርሱም ተዘግቶ ነበርና። በእግዚአብሔር ቤት በመቅደሱ ውስጥ እንገናኝ የመቅደሱንም ደጆች እንዝጋ፤ እነርሱ መጥተው ይገድሉሃልና፥ በሌሊትም ይገድሉህ ዘንድ ይመጣሉና አለ።
11. እኔም። እንደ እኔ ያለ ሰው የሸሸና፥ ነፍሱንስ ያድን ዘንድ ወደ መቅደስ የገባ ማን ነው? እኔስ አልገባም አልሁት።
12. እግዚአብሔርም ልኮት እንዳልነበረ፥ በእኔ ላይ ግን ትንቢት እንደ ተናገረ፥ እነሆ፥ አወቅሁ፤ ጦብያና ሰንባላጥም ገዝተውት ነበር።
13. ይህንም ነገር አደርግና እበድል ዘንድ፥ በእኔም ላይ ክፋት እንዲናገሩና እንዲያላግጡ ያስፈራራኝ ዘንድ ተገዝቶ ነበር።
14. አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ ሥራቸው ጦብያንና ሰንባላጥን ያስፈራሩኝም ዘንድ የወደዱትን ነቢይቱን ኖዓድያን የቀሩትንም ነቢያት አስብ።
15. ቅጥሩም በኤሉል ወር በሀያ አምስተኛው ቀን በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጨረሰ።
16. ጠላቶቻችንም ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ በዙሪያችን የነበሩ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፥ በራሳቸውም አሳብ እጅግ ተዋረዱ፥ ይህም ሥራ በእግዚአብሔር እንደ ተደረገ አወቁ።
18. ጦብያም የኤራ ልጅ የሴኬንያ አማች ስለ ነበረ፥ ልጁም ይሆሐናን የቤራክያን ልጅ የሜሱላምን ሴት ልጅ ስላገባ፥ በይሁዳ ብዙ ሰዎች ከእርሱ ጋር ተማምለው ነበርና በዚያ ወራት ብዙ የይሁዳ አለቆች ወደ ጦብያ ደብዳቤዎች ይልኩ ነበር፥ የጦብያም ደብዳቤዎች ወደ እነርሱ ይመጡ ነበር።
19. ደግሞም በፊቴ ስለ እርሱ መልካም ይናገሩ ነበር፥ ቃሌንም ያወሩለት ነበር፤ ጦብያም ሊያስፈራራኝ ደብዳቤዎችን ይልክ ነበር።

  Nehemiah (6/13)