Nehemiah (2/13)  

1. በንጉሡ በአርጤክስስ በሀያኛው ዓመት በኒሳን ወር የወይን ጠጅ በፊቱ በነበረ ጊዜ ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ቀድሞ ግን በፊቱ ያለ ኃዘን እኖር ነበር።
2. ንጉሡም። ሳትታመም ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ኅዘን ነው እንጂ ሌላ ነገር አይደለም አለኝ። እጅግም ብዙ አድርጌ ፈራሁ።
3. ንጉሡንም። ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ፤ የአባቶቼ መቃብር ያለባት ከተማ ተፈትታለችና፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋልና ፊቴ ስለ ምን አይዘን? አልሁት።
4. ንጉሡም። ምን ትለምነኛለህ? አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ።
5. ንጉሡንም። ንጉሡን ደስ ቢያሰኝህ፥ ባሪያህም በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፥ እሠራው ዘንድ ወደ ይሁዳ ወደ አባቶቼ መቃብር ከተማ ስደደኝ አልሁት።
6. ንግሥቲቱም በአጠገቡ ተቀምጣ ሳለች ንጉሡ። መንገድህ እስከ መቼ ድረስ ይሆናል? መቼስ ትመለሳለህ? አለኝ። ንጉሡም ይሰድደኝ ዘንድ ደስ አለው፤ እኔም ዘመኑን ቀጠርሁለት።
7. ንጉሡንም። ንጉሡ ደስ ቢለው፥ እስከ ይሁዳ አገር እንዲያደርሱኝ በወንዝ ማዶ ላሉት ገዦች ደብዳቤ ይሰጠኝ፤
8. በቤቱም አጠገብ ላለው ለግንብ በሮች፥ ለከተማውም ቅጥር፥ ለምገባበትም ቤት እንጨት እንዲሰጠኝ ለንጉሡ ዱር ጠባቂ ለአሳፍ ደብዳቤ ይሰጠኝ አልሁት። ንጉሡም በእኔ ላይ መልካም እንደ ሆነችው እንደ አምላኬ እጅ ሰጠኝ።
9. በወንዙም ማዶ ወዳሉት አለቆች መጥቼ የንጉሡን ደብዳቤ ሰጠኋቸው ንጉሡም ከእኔ ጋር የሠራዊቱን አለቆችና ፈረሰኞች ሰደደ።
10. ሖሮናዊውም ሰንባላጥና ባሪያው አሞናዊ ጦብያ ለእስራኤል ልጆች መልካምን ነገር የሚሻ ሰው እንደ መጣ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተበሳጩ።
11. ወደ ኢየሩሳሌምም ደረስሁ፥ በዚያም ሦስት ቀን ያህል ተቀመጥሁ።
12. በሌሊትም ተነሣሁ፥ ከእኔም ጋር አያሌ ሰዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርም ለኢየሩሳሌም አደርገው ዘንድ በልቤ ያኖረውን ለማንም አላስታወቅሁም፤ ተቀምጬበት ከነበረው እንስሳ በቀር ከእኔ ጋር ምንም እንስሳ አልነበረም።
13. በሸለቆውም በር ወጣሁ፥ ወደ ዘንዶውም ምንጭና ወደ ጕድፍ መጣያው በር ሄድሁ፤ የፈረሰውንም የኢየሩሳሌምን ቅጥር፥ በእሳትም የተቃጠሉትን በሮችዋን ተመለከትሁ።
14. ወደ ምንጩም በርና ወደ ንጉሡ መዋኛ አለፍሁ፤ ተቀምጬበትም የነበረው እንስሳ የሚያልፍበት ስፍራ አልነበረም።
15. በሌሊትም በፈፋው በኩል ወጥቼ ቅጥሩን ተመለከትሁ፤ ዘወርም ብዬ በሸለቆው በር ገባሁ፥ እንዲሁም ተመለስሁ።
16. ሹማምቱ ግን ወዴት እንደ ሄድሁ፥ ምን እንዳደረግሁም አላወቁም ነበር፤ ለአይሁድና ለካህናቱ፥ ለታላላቆችና ለሹማምቱም፥ ሥራም ይሠሩ ለነበሩት ለሌሎች ገና አልተናገርሁም ነበር።
17. እኔም። እኛ ያለንበትን ጕስቍልና ኢየሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮችዋም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ፤ አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ አልኋቸው።
18. የአምላኬም እጅ በእኔ ላይ መልካም እንደሆነች፥ ንጉሡም የነገረኝን ቃል ነገርኋቸው። እነርሱም። እንነሣና እንሥራ አሉ። እጃቸውንም ለበጎ ሥራ አበረቱ።
19. ሖሮናዊውም ሰንባላጥ፥ ባሪያውም አሞናዊው ጦብያ፥ ዓረባዊውም ጌሳም በሰሙ ጊዜ በንቀት ሳቁብን፥ ቀላል አድርገውንም። ይህ የምታደርጉት ነገር ምንድር ነው? በውኑ በንጉሡ ላይ ትሸፍቱ ዘንድ ትወድዳላችሁን? አሉ።
20. እኔም መልሼ። የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም እድል ፈንታና መብት መታሰቢያም የላችሁም አልኋቸው።

  Nehemiah (2/13)