Nehemiah (1/13)  

1. የሐካልያ ልጅ የነህምያ ቃል። በሀያኛው ዓመት በካሴሉ ወር እንዲህ ሆነ፤
2. እኔ በሱሳ ግንብ ሳለሁ፥ ከወንድሞቼ አንዱ አናኒ ከእርሱም ጋር ሌሎች ሰዎች ከይሁዳ መጡ፤ እኔም የዳኑትን ከምርኮ የተረፉትን የአይሁድን ነገር የኢየሩሳሌምንም ነገር ጠየቅኋቸው።
3. እነርሱም። በዚያ ስፍራ ያሉት ከምርኮ የተረፉት ቅሬታዎች በታላቅ መከራና ስድብ አሉ፤ የኢየሩሳሌምም ቅጥር ፈርሶአል፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋል አሉኝ።
4. ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፥ አያሌ ቀንም አዝን ነበር፤ በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር፥
5. እንዲህም አልሁ። አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ፥ ለሚወድዱህና ትእዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ፥
6. እኔ ባሪያህ ዛሬ በፊትህ ስለ ባሪያዎችህ ስለ እስራኤል ልጆች ሌሊትና ቀን የምጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ጆሮህ ያድምጥ፥ ዓይኖችህም ይከፈቱ፤ በአንተ ላይም ያደረግነውን የእስራኤልን ልጆች ኃጢአት እናዘዝልሃለሁ፤ እኔና የአባቴም ቤት በድለናል።
7. እኛም በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሠርተናል፤ ለባሪያህም ለሙሴ ያዘዝኸውን ትእዛዝና ሥርዓት ሕግም አልጠበቅንም።
9. አሁንም ብትተላለፉ በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ወደ እኔ ብትመለሱ ግን ትእዛዜንም ብትጠብቁ ብታደርጓትም፥ ከእናንተ ሰዎች እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ምንም ቢበተኑ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፥ ስሜም ይኖርበት ዘንድ ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ ብለህ ለባሪያህ ለሙሴ ያዘዝኸውን ቃል እባክህ አስብ።
10. እነዚህም በታላቅ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዠሃቸው ባሪያዎችህና ሕዝብህ ናቸው።
11. ጌታ ሆይ፥ ጆሮህ የባሪያህን ጸሎት፥ ስምህንም ይፈሩ ዘንድ የሚወድዱትን፥ የባሪያዎችህን ጸሎት ያድምጥ፤ ዛሬም ለባሪያህ አከናውንለት፥ በዚህም ሰው ፊት ምሕረትን ስጠው። እኔም ለንጉሡ ጠጅ አሳላፊው ነበርሁ።

      Nehemiah (1/13)