Nahum (3/3)    

1. ለደም ከተማ ወዮላት! በሁለንተናዋ ሐሰትና ቅሚያ ሞልቶባታል፤ ንጥቂያ ከእርስዋ አያልቅም።
2. የአለንጋ ድምፅ፥ የመንኰራኵርም ድምፅ፥ የፈረሶችም ኮቴ፥ የፈጣን ሰረገላም ጩኸት ተሰምቶአል፤
3. ፈረሰኛው ይጋልባል፥ ሰይፍም ይንቦገቦጋል፥ ጦርም ይብለጨለጫል፤ የተገደሉትም ይበዛሉ፥ በድኖችም በክምር ይከመራሉ፥ ሬሳቸውም አይቈጠርም፤ በሬሳቸውም ይሰናከላሉ።
4. ስለ ተዋበችው ጋለሞታ ግልሙትና ብዛት ይህ ሆኖአል፤ እርስዋም በመተትዋ እጅግ በለጠች፥ አሕዛብንም በግልሙትናዋ፥ ወገኖችንም በመተትዋ ሸጠች።
5. እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ልብስሽን በፊትሽ እገልጣለሁ፤ ኅፍረተ ሥጋሽንም ለአሕዛብ፥ ነውርሽንም ለመንግሥታት አሳያለሁ።
6. ርኵሰትንም በላይሽ እጥላለሁ፥ እንቅሻማለሁ፥ ማላገጫም አደርግሻለሁ።
7. የሚያይሽም ሁሉ ከአንቺ ሸሽቶ። ነነዌ ባድማ ሆናለች፤ የሚያለቅስላትስ ማን ነው? የሚያጽናናትንስ ከወዴት እፈልጋለሁ? ይላል።
8. አንቺ በመስኖች መካከል ከተቀመጠችው፥ ውኃም በዙሪያዋ ከነበራት፥ ምሽግዋም ባሕር ከነበረ፥ ቅጥርዋም በባሕር ውስጥ ከነበረ ከኖእ አሞን ትበልጫለሽን?
9. ኢትዮጵያና ግብጽ የማይቈጠር ኃይልዋ ነበሩ፤ ፉጥና ልብያ ረዳቶችዋ ነበሩ።
10. እርስዋ ግን ተማርካ ፈለሰች፤ ሕፃናቶችዋ በመንገድ ሁሉ ራስ ላይ ተፈጠፈጡ፤ በከበርቴዎችዋም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፥ ታላላቆችዋም ሁሉ በሰንሰለት ታሰሩ።
11. አንቺም ትሰክሪአለሽ ወራዳም ትሆኛለሽ፤ አንቺ ደግሞ ከጠላት የተነሣ መጠጊያን ትፈልጊአለሽ።
12. አምባሽ ሁሉ የመጀመሪያውን የበሰለ ፍሬ እንደ ያዙ እንደ በለስ ዛፎች ነው፤ ቢወዛወዝ በሚበላው አፍ ውስጥ ይወድቃል።
13. እነሆ፥ በመካከልሽ ያሉ ሕዝብሽ ሴቶች ናቸው፤ የአገርሽ በሮች ለጠላቶችሽ ፈጽሞ ተከፍተዋል፥ እሳትም መወርወሪያዎችህን በልቶአል።
14. ከብበው ያስጨንቁሻልና ውኃን ቅጂ፤ አምባሽን አጠንክሪ፤ ወደ ጭቃ ገብተሽ እርገጪ፤ የጡብን መሠሪያ ያዢ።
15. በዚያ እሳት ይበላሻል፥ ሰይፍ ያጠፋሻል፥ እንደ ደጎብያ ይበላሻል፤ እንደ ደጎብያ ብዢ፥ እንደ አንበጣም ተባዢ።
16. ነጋዴዎችሽን ከሰማይ ከዋክብት ይልቅ አበዛሽ፤ ደጎብያ ተዘረጋ፥ በረረም።
17. በአንቺ ዘንድ ዘውድ የጫኑት እንደ አንበጣ፥ አለቆችሽም እንደሚንቀሳቀሱ ኩብኩባዎች ናቸው፤ በብርድ ቀን በቅጥር ውስጥ ይቀመጣሉ፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ያኰበኵባሉ፤ ስፍራቸው በየት እንደ ሆነ አይታወቅም።
18. የአሦር ንጉሥ ሆይ፥ እረኞችህ አንቀላፍተዋል፤ መኳንንቶችህም ዐርፈዋል፤ ሕዝብህም በተራሮች ላይ ተበትኖአል፥ የሚሰበስበውም የለም።
19. ስብራትህ አይፈወስም፥ ቍስልህም ክፉ ነው፤ ወሬህንም የሚሰሙ ሁሉ እጃቸውን በአንተ ላይ ያጨበጭባሉ፤ ክፋትህ ሁልጊዜ ያላለፈችበት ሰው ማን ነውና?

  Nahum (3/3)