| ← Nahum (2/3) → |
| 1. | የሚቀጠቅጥ በአንተ ላይ ወጥቶአል፤ ምሽግን ጠብቅ፥ መንገድንም ሰልል፤ ወገብህን አጽና፥ ኃይልህንም እጅግ አበርታ። |
| 2. | ዘራፊዎች ዘርፈዋቸዋልና፥ የወይናቸውንም አረግ አጥፍተዋልና እግዚአብሔር የያዕቆብን ክብር እንደ እስራኤል ክብር ይመልሳል። |
| 3. | የኃያላኑ ጋሻ ቀልቶአል፥ ጽኑዓንም ቀይ ልብስ ለብሰዋል። እርሱም በሚያዘጋጅበት ቀን ሰረገሎች እንደ እሳት ይንቦገቦጋሉ፤ የጦሩም ሶመያ ይወዛወዛል። |
| 4. | ሰረገሎች በመንገድ ላይ ይነጕዳሉ፥ አደባባይም ይጋጫሉ፤ መልካቸው እንደ ፋና ነው፥ እንደ መብረቅም ይከንፋሉ። |
| 5. | መሳፍንቱን ያስባል፤ በአረማመዳቸው ይሰናከላሉ፤ ፈጥነው በቅጥርዋ ላይ ይወጣሉ፥ መጠጊያም ተዘጋጀለት። |
| 6. | የወንዞቹም መዝጊያዎች ተከፈቱ፥ የንጉሡ ቤትም ቀለጠች። |
| 7. | ንግሥት ተገለጠች፥ ተማረከችም፥ ሴቶች ባሪያዎችዋም እንደ ርግብ እየጮኹና ደረታቸውን እየመቱ ዋይ ዋይ ይላሉ። |
| 8. | ነነዌ ግን ከዱሮ ዘመን ጀምራ እንደ ተከማቸ ውኃ ነበረች፤ አሁን ግን ይሸሻሉ፤ እነርሱም። ቁሙ፥ ቁሙ ይላሉ፥ ነገር ግን የሚመለስ የለም። |
| 9. | መዝገብዋ መጨረሻ የለውምና፥ የከበረውም የዕቃዋ ሁሉ ብዛት አይቈጠርምና ብሩን በዝብዙ፥ ወርቁንም በዝብዙ። |
| 10. | ባዶና ባድማ ምድረ በዳም ሆናለች፤ ልብ ቀልጦአል፥ ጕልበቶችም ተብረክርከዋል፤ በወገብም ሁሉ ሕማም አለ፥ የሰዎችም ሁሉ ፊት ጠቍሮአል። |
| 11. | የአንበሾችም መደብ፥ የአንበሾችም ደቦል የሚሰማራበት፥ አንበሳውና አንበሳይቱ ግልገሉም ሳይፈሩ የሚሄዱት ስፍራ ወዴት ነው? |
| 12. | አንበሳው ለልጆቹ የሚበቃውን ነጠቀ፥ ለእንስቶቹም ሰበረላቸው ዋሻውን በንጥቂያ፥ መደቡንም በቅሚያ ሞልቶታል። |
| 13. | እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ሰረገሎችዋንም አቃጥዬ አጤሳለሁ፥ ሰይፍም የአንበሳ ደቦሎችሽን ይበላቸዋል፤ ንጥቂያሽንም ከምድር አጠፋለሁ፥ የመልክተኞችሽን ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ አይሰማም። |
| ← Nahum (2/3) → |