Nahum (1/3)  

1. ስለ ነነዌ የተነገረ ሸክም፤ የኤልቆሻዊው የናሆም የራእዩ መጽሐፍ ይህ ነው።
2. እግዚአብሔር ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው፤ እግዚአብሔር ተበቃይና መዓትን የተሞላ ነው፤ እግዚአብሔር ተቃዋሚዎቹን ይበቀላል፥ ለጠላቶቹም ቍጣውን ይጠብቃል።
3. እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ በደለኛውንም። ንጹሕ ነህ አይልም፤ እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።
4. ባሕሩንም ይገሥጻታል፥ ያደርቃትማል፥ ወንዞችንም ሁሉ ያደርቃል፤ ባሳንና ቀርሜሎስም ላልተዋል፥ የሊባኖስም አበባ ጠውልጎአል።
5. ተራሮችም ከእርሱ የተነሣ ታወኩ፥ ኮረብቶችም ቀለጡ፤ ምድርና ዓለም የሚኖሩበትም ሁሉ ከፊቱ ተናወጡ።
6. በቍጣው ፊት የሚቆም ማን ነው? የቍጣውንም ትኵሳት ማን ይታገሣል? መዓቱ እንደ እሳት ይፈስሳል፥ ከእርሱም የተነሣ ዓለቶች ተሰነጠቁ።
7. እግዚአብሔር መልካም ነው፥ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል።
8. ስፍራዋን ግን በሚያጥለቀልቅ ጎርፍ ፈጽሞ ያጠፋታል፥ ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል።
9. በእግዚአብሔር ላይ የምታስቡት ምንድር ነው? እርሱ ፈጽሞ ያጠፋል፥ መከራም ሁለተኛ አይነሣም።
10. እርስ በእርሳቸው እንደ ተመሰቃቅለ እሾህ ቢሆኑ፥ በመጠጣቸውም ቢሰክሩ እንደ ደረቅ ገለባ ፈጽመው ይጠፋሉ።
11. በእግዚአብሔር ላይ በክፉ የሚያስብ፥ ክፋትን የሚመክር፥ ከአንተ ዘንድ ወጥቶአል።
12. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ኃይለኞችና ብዙዎች ቢሆኑ እንዲሁ ይቈረጣሉ፥ እርሱም ያልቃል። እኔም አስጨንቄሃለሁ፥ ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ አላስጨንቅህም።
13. አሁንም ቀንበሩን ከአንተ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ።
14. እግዚአብሔርም ከስምህ ማንም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይዘራ ስለ አንተ አዝዞአል፤ ከአምላኮችህ ቤት የተቀረጸውንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል አጠፋለሁ፤ አንተም የተጠቃህ ነህና መቃብርህን እምሳለሁ።
15. እነሆ፥ የምስራችን የሚያመጣ ሰላምንም የሚያወራ ሰው እግር በተራሮች ላይ ነው! ይሁዳ ሆይ፥ አጥፊው ፈጽሞ ጠፍቶአልና፥ ከእንግዲህም ወዲህ በአንተ ዘንድ አያልፍምና ዓመት በዓሎችህን አድርግ፥ ስእለቶችህን ክፈል።

      Nahum (1/3)