← Micah (7/7) |
1. | የዛፍ ፍሬና የወይን ፍሬ ከተለቀሙ በኋላ እንደ ቀረው ቃርሚያ ሆኛለሁና ወዮልኝ! መብል የሚሆን ዘለላ፥ ነፍሴም የተመኘችው በመጀመሪያ የበሰለው በለስ የለም። |
2. | ደግ ሰው ከምድር ጠፍቶአል፥ በሰውም መካከል ቅን የለም፤ ሁሉ ደምን ለማፍሰስ ያደባሉ፥ ሰውም ሁሉ ወንድሙን በመረብ ለመያዝ ይከታተለዋል። |
3. | እጆቻቸውን ለክፋት ያነሣሉ፤ አለቃውና ፈራጁ ጉቦን ይፈልጋሉ፥ ትልቁም ሰው እንደ ነፍሱ ምኞት ይናገራል፤ እንዲሁም ክፋትን ይጐነጕናሉ። |
4. | ከእነርሱም ሁሉ የተሻለው እርሱ እንደ አሜከላ ነው፥ ከሁሉም ቅን የሆነው እንደ ኵርንችት ነው፤ ጠባቆችህ የሚጐበኙበት ቀን መጥቶአል፤ አሁን ይሸበራሉ። |
5. | ባልንጀራን አትመኑ፥ በወዳጅም አትታመኑ፤ የአፍህን ደጅ በብብትህ ከምትተኛው ጠብቅ። |
6. | ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃልና፥ ሴት ልጅ በእናትዋ ላይ፥ ምራቲቱም በአማትዋ ላይ ትነሣለችና፥ የሰው ጠላቶች የቤቱ ሰዎች ናቸውና። |
7. | እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እመለከታለሁ፥ የመድኃኒቴንም አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አምላኬም ይሰማኛል። |
8. | ጠላቴ ሆይ፥ ብወድቅ እነሣለሁና፥ በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና በእኔ ላይ ደስ አይበልሽ። |
9. | በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁና እስኪምዋገትልኝ ድረስ፥ ፍርድን ለእኔ እስኪያደርግ ድረስ ቍጣውን እታገሣለሁ። ወደ ብርሃን ያወጣኛል፥ ጽድቅንም አያለሁ። |
10. | ጠላቴም ታያለች፥ እኔንም። አምላክህ እግዚአብሔር ወዴት ነው? ያለች በእፍረት ትከደናለች። |
11. | ዓይኖቼ ይመለከቱአታል፤ አሁን እንደ መንገድ ጭቃ ትረገጣለች። ቅጥርሽ በሚሠራበት በዚያ ቀን ድንበርሽ ትስፋፋለች። |
12. | በዚያ ቀን ከአሦርና ከግብጽ ከተሞች፥ ከግብጽ እስከ ወንዙ፥ ከባሕርም እስከ ባሕር፥ ከተራራም እስከ ተራራ ድረስ ወደ አንቺ ይመጣሉ። |
13. | ምድሪቱ ግን በሚኖሩባት በሥራቸው ፍሬ ምክንያት ባድማ ትሆናለች። |
14. | በቀርሜሎስ መካከል ባለው ዱር ብቻቸውን የተቀመጡት ሰዎችህ፥ የርስትህን በጎች፥ በበትርህ አግድ፤ እንደ ቀደመውም ዘመን በበሳንና በገለዓድ ይሰማሩ። |
15. | ከግብጽ ምድር እንደ ወጣህበት ዘመን ተአምራትን አሳያቸዋለሁ። |
16. | አሕዛብ አይተው በጕልበታቸው ሁሉ ያፍራሉ፤ እጃቸውን በአፋቸው ላይ ያኖራሉ፥ ጆሮአቸውም ትደነቍራለች፤ |
17. | እንደ እባብም መሬት ይልሳሉ፥ እንደ ምድርም ተንቀሳቃሾች እየተንቀጠቀጡ ከግንባቸው ይመጣሉ፤ ፈርተውም ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመጣሉ፥ ስለ አንተም ይፈራሉ። |
18. | በደልን ይቅር የሚል፥ የርስቱንም ቅሬታ ዓመፅ የሚያሳልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረትን ይወድዳልና ቍጣውን ለዘላለም አይጠብቅም። |
19. | ተመልሶ ይምረናል፤ ክፋታችንንም ይጠቀጥቃል፥ ኃጢአታችንንም በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል። |
20. | ከቀድሞ ዘመን ጀምረህ ለአባቶቻችን የማልህላቸውን እውነት ለያዕቆብ፥ ምሕረትንም ለአብርሃም ታደርጋለህ። |
← Micah (7/7) |