Micah (6/7)  

1. አሁን። ተነሣ፥ በተራሮችም ፊት ተፋረድ፥ ኮረብቶችም ቃልህን ይስሙ ብሎ እግዚአብሔር የሚለውን ስሙ።
2. ተራሮች ሆይ፥ ጠንካሮች የምድር መሠረቶችም ሆይ፥ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ክርክር አለውና፥ ከእስራኤልም ጋር ይፋረዳልና የእግዚአብሔርን ክርክር ስሙ።
3. ሕዝቤ ሆይ፥ ምን አድርጌሃለሁ? በምንስ አድክሜሃለሁ? መስክርብኝ።
4. ከግብጽ ምድር አውጥቼሃለሁ፥ ከባርነት ቤትም ተቤዥቼሃለሁ፤ በፊትህም ሙሴንና አሮንን ማርያምንም ልኬልህ ነበር።
5. ሕዝቤ ሆይ፥ የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ የመከረውን፥ የቢዖርም ልጅ በለዓም የመለሰለትን አሁን አስብ፤ የእግዚአብሔርንም የጽድቅ ሥራ ታውቅ ዘንድ ከሰጢም ጀምሮ እስከ ጌልገላ ድረስ አስብ።
6. ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን?
7. እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጎች ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? ወይስ የበኵር ልጄን ስለ በደሌ፥ የሆዴንም ፍሬ ስለ ነፍሴ ኃጢአት እሰጣለሁን?
8. ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?
9. የእግዚአብሔር ድምፅ ከተማይቱን ይጠራታል፤ ስምህን መፍራት ጥበብ ነው፤ የመቅሠፍትን በትር፥ እርሱንም ያዘጋጀ ማን እንደ ሆነ ስሙ።
10. በውኑ በኃጢአተኛ ቤት የኃጢአት መዝገብ፥ የተጸየፈም ውሽተኛ መስፈሪያ ገና አለ ይሆን?
11. በአባይ ሚዛንና በከረጢት ባለ በተንኰል መመዘኛ ንጹሕ እሆናለሁን?
12. ባለ ጠጎችዋን ግፍ ሞልቶባቸዋል፤ በእርስዋም የሚኖሩ በሐሰት ተናግረዋል፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ተንኰለኛ ነው።
13. ስለዚህ እኔ ደግሞ በክፉ ቍስል መታሁህ፤ ስለ ኃጢአትህም አፈርስሁህ።
14. ትበላለህ፥ ነገር ግን አትጠግብም፥ ችጋርህም በመካከልህ ይሆናል፤ ትወስዳለህ፥ ነገር ግን አታድንም፤ የምታድነውንም ለሰይፍ እሰጣለሁ።
15. ትዘራለህ፥ ነገር ግን አታጭድም፤ ወይራውንም ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን ዘይቱን አትቀባም፤ ወይኑንም ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን የወይን ጠጁን አትጠጣም።
16. አንተን ለጥፋት፥ በእርስዋም የሚኖሩትን ለማፍዋጫ እሰጥ ዘንድ የዘንበሪን ሥርዓትና የአክዓብን ቤት ሥራ ሁሉ ጠብቃችኋል፥ በምክራቸውም ሄዳችኋል፤ የሕዝቤንም ስድብ ትሸከማላችሁ።

  Micah (6/7)