| ← Micah (4/7) → | 
| 1. | በመጨረሻውም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አሕዛብም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። | 
| 2. | ከጽዮን ሕግ፥ ከኢየሩሳሌምም የእግዚአብሔር ቃል ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው። ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በፍለጋውም እንሄዳለን ይላሉ። | 
| 3. | በብዙዎችም አሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች አሕዛብ ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፥ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም ከእንግዲህም ወዲህ ሰልፍ አይማሩም። | 
| 4. | የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፥ የሚያስፈራውም የለም። | 
| 5. | ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል፥ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን። | 
| 6. | በዚያ ቀን አንካሳይቱን እሰበስባለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የባከነችውንና ያስጨነቅኋትንም አከማቻለሁ፤ | 
| 7. | አንካሳይቱንም ለቅሬታ፥ ወደ ሩቅም የተጣለችውን ለብርቱ ሕዝብ አደርጋታለሁ፤ ከዚያም ወዲያ እስከ ዘላለም ድረስ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል። | 
| 8. | አንተም የመንጋ ግንብ ሆይ፥ የጽዮን ሴት ልጅ አምባ፥ ወደ አንተ ትመጣለች፤ የቀደመችው ግዛት፥ የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ መንግሥት ትደርሳለች። | 
| 9. | አሁንስ ለምን ትጮኺአለሽ? እንደምትወልድ ሴት ምጥ የደረሰብሽ፥ ንጉሥ ስለሌለሽ ነውን? ወይስ መካሪ ስለ ጠፋብሽ ነውን? | 
| 10. | የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እንደምትወልድ ሴት አምጠሽ ውለጂ፤ አሁን ከከተማ ትወጫለሽና፥ በሜዳም ትቀመጫለሽ፥ ወደ ባቢሎንም ትደርሻለሽ፤ በዚያም ያድንሻል፥ በዚያም እግዚአብሔር ከጠላቶችሽ እጅ ይቤዥሻል። | 
| 11. | አሁንም። ርኩስ ትሁን፥ ዓይናችንም በጽዮን ላይ ይይ የሚሉ ብዙ አሕዛብ በአንቺ ላይ ተሰብስበዋል። | 
| 12. | ነገር ግን የእግዚአብሔርን አሳብ አያውቁም፥ ምክሩንም አያስተውሉም፤ እንደ ነዶ ወደ አውድማ አከማችቶአቸዋልና። | 
| 13. | የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ቀንድሽን ብረት፥ ጥፍርሽንም ናስ አደርጋለሁና ተነሺ አሂጂ፤ ብዙ አሕዛብንም ታደቅቂአለሽ፤ ትርፋቸውንም ለእግዚአብሔር፥ ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ ትቀድሻለሽ። | 
| ← Micah (4/7) → |