Micah (2/7)  

1. በመኝታቸው ላይ በደልን ለሚያስቡ ክፋትንም ለሚያደርጉ ወዮላቸው! ኃይል በእጃቸው ነውና ሲነጋ ይፈጽሙታል።
2. በእርሻው ላይ ይመኛሉ፥ በግዴታም ይይዙታል፤ በቤቶችም ላይ ይመኛሉ፥ ይወስዱአቸውማል፤ ሰውንና ቤቱን፥ ሰውንና ርስቱንም ይነጥቃሉ።
3. ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በዚህ ወገን ላይ በክፉ አስባለሁ፥ ከዚያም አንገታችሁን አታነሡም፤ ዘመኑም ክፉ ነውና ቀጥ ብላችሁ አትሄዱም።
4. በዚያ ቀን በምሳሌ ይመስሉባችኋል፥ በጽኑ ልቅሶም ያለቅሱላችኋል፤ እነርሱም። ፈጽመን ጠፍተናል፤ የሕዝቤን እድል ፈንታ ይሰፍራል፥ እርሱንም የሚከለክል የለም፤ እርሻችንን ለዓመፀኞች ይከፍላል ይላሉ።
5. ስለዚህ በእግዚአብሔር ጉባኤ መካከል በዕጣ ገመድ የሚጥል አይኖርህም።
6. ትንቢት አትናገሩ ብለው ይናገራሉ፤ በእነዚህ ላይ ትንቢት አይናገሩም፥ ስድብም አይርቅም።
7. የያዕቆብ ቤት የተባልህ ሆይ፥ በውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ የማይታገሥ ነውን? ወይስ ሥራው እንደዚች ናትን? ቃሌስ በቅን ለሚሄድ በጎነት አያደርግምን?
8. ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ሕዝቤ እንደ ጠላት ሆኖ ተነሥቶአል፤ ቀሚስንና መጐናጸፊያን ገፈፋችሁ፤ ሳይፈሩም፤ የሚያልፉትን ከሰልፍ እንደሚመለሱ አደረጋችኋቸው።
9. የሕዝቤንም ሴቶች ከተሸለሙ ቤቶቻቸው አሳደዳችኋቸው፤ ከሕፃናቶቻቸውም ክብሬን ለዘላለም ወሰዳችሁ።
10. በዚህ ዕረፍት የላችሁምና ተነሥታችሁ ሂዱ፤ በርኵሰት ምክንያት ክፉ ጥፋት ታጠፋችኋለች።
11. ነፋስንም ተከትሎ። ስለ ወይን ጠጅና ስለ ስካር ትንቢት እናገርልሃለሁ ብሎ ሐሰትን የሚናገር ሰው ቢኖር እርሱ ለዚህ ሕዝብ ነቢይ ይሆናል።
12. ያዕቆብ ሆይ፥ ሁለንተናህን ፈጽሞ እሰበስባለሁ፥ የእስራኤልንም ቅሬታ ፈጽሞ አከማቻለሁ፤ እንደ ባሶራ በጎችና እንደ መንጋ በማሰማርያቸው ውስጥ በአንድነት አኖራቸዋለሁ፤ ከሰው ብዛት የተነሣ ድምፃቸውን ያሰማሉ።
13. ሰባሪው በፊታቸው ወጥቶአል፤ እነርሱም ሰብረው ወደ በሩ አልፈዋል፥ በእርሱም በኩል ወጥተዋል፤ ንጉሣቸውም በፊታቸው አልፎአል፥ እግዚአብሔርም በራሳቸው ላይ ነው።

  Micah (2/7)