Micah (1/7) → |
1. | በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታምና በአካዝ በሕዝቅያስም ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው፥ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው፥ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። |
2. | እናንተ አሕዛብ ሁሉ፥ ስሙ፤ ምድርም ሙላዋም ታድምጥ፤ ጌታ እግዚአብሔርም፥ እርሱም በቅዱስ መቅደሱ የሆነ ጌታ፥ ይመስክርባችሁ። |
3. | እነሆ፥ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፥ ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይረግጣል። |
4. | ተራሮችም በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፥ በገደልም ወርዶ እንደሚፈስስ ውኃ፥ በበታቹ ይቀልጣሉ፥ ሸለቆችም ይሰነጠቃሉ። |
5. | ይህ ሁሉ ስለ ያዕቆብ በደልና ስለ እስራኤል ቤት ኃጢአት ነው። የያዕቆብም በደል ምንድር ነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኮረብታው መስገጃ ምንድር ነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን? |
6. | ስለዚህ ሰማርያን በሜዳ እንደሚገኝ የድንጋይ ክምር፥ ወይን እንደሚተከልበትም ስፍራ አደርጋታለሁ፤ ድንጋዮችዋንም ወደ ሸለቆ እወረውራለሁ፥ መሠረቶችዋንም እገልጣለሁ። |
7. | የተቀረጹትም ምስሎችዋ ይደቅቃሉ፥ በግልሙትና ያገኘችው ዋጋ ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፥ ጣዖታትዋንም ሁሉ አጠፋለሁ፤ በግልሙትና ዋጋ ሰበሰበቻቸው፥ ወደ ግልሙትናም ዋጋ ይመለሳሉና። |
8. | ስለዚህ ነገር ዋይ ብላ ታለቅሳለች፥ ባዶ እግርዋንና ዕራቁትዋን ሆና ትሄዳለች፤ እንደ ቀበሮ ታለቅሳለች፥ እንደ ሰጐንም ዋይ ትላለች፤ |
9. | ቍስልዋ የማይፈወስ ነውና፤ እስከ ይሁዳም ደርሶአልና፥ ወደ ሕዝቤም በር ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦአልና። |
10. | በጌት ላይ አታውሩ፤ በአኮ ላይ እንባን አታድርጉ፤ በቤትዓፍራ በትቢያ ላይ ተንከባለሉ። |
11. | በሻፊር የምትቀመጪ ሆይ፥ በዕራቁትነትሽና በእፍረት እለፊ፤ በጸዓናን የምትቀመጠው አልወጣችም፤ የቤትኤጼል ልቅሶ ከእናንተ ዘንድ መኖሪያውን ይወስዳል። |
12. | ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ እስከ ኢየሩሳሌም በር ድረስ ወርዶአልና በማሮት የምትቀመጠው በጎነትን ትጠባበቃለች። |
13. | በለኪሶ የምትቀመጪ ሆይ፥ ሰረገላውን ለፈረስ እሰሪ፤ እርስዋ ለጽዮን ሴት ልጅ የኃጢአት መጀመሪያ ነበረች፤ የእስራኤል በደል በአንቺ ዘንድ ተገኝቶአልና። |
14. | ስለዚህ ትሎት ለሞሬሼትጌት ትሰጪአለሽ፤ የአክዚብ ቤቶች ለእስራኤል ነገሥታት አታላይ ይሆናሉ። |
15. | በመሪሳ የምትቀመጪ ሆይ፥ ወራሽ አመጣብሻለሁ፤ የእስራኤል ክብር ወደ ዓዶላም ይመጣል። |
16. | ተማርከው ከአንቺ ዘንድ ወጥተዋልና ስለ ተድላሽ ልጆች ራስሽን ንጪ፥ ጠጕርሽንም ተቈረጪ፤ ቡሃነትሽንም እንደ ንስር አስፊ። |
Micah (1/7) → |