← Matthew (28/28) |
1. | በሰንበትም መጨረሻ መጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። |
2. | እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። |
3. | መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። |
4. | ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ሆኑ። |
5. | መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ |
6. | እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። |
7. | ፈጥናችሁም ሂዱና። ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። |
8. | እነሆም፥ ነገርኋችሁ። በፍርሃትና በታላቅ ደስታም ፈጥነው ከመቃብር ሄዱ፥ ለደቀ መዛሙርቱም ሊያወሩ ሮጡ። |
9. | እነሆም፥ ኢየሱስ አገኛቸውና። ደስ ይበላችሁ አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። |
10. | በዚያን ጊዜ ኢየሱስ። አትፍሩ፤ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ፥ በዚያም ያዩኛል አላቸው። |
11. | ሲሄዱም ሳሉ እነሆ፥ ከጠባቆቹ አንዳንድ ወደ ከተማ መጥተው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩ። |
12. | ከሽማግሎች ጋርም ተሰብስበው ተማከሩና ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተዋቸው። |
13. | እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ። |
14. | ይህም በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደ ሆነ፥ እኛ እናስረዳዋለን እናንተም ያለ ሥጋት እንድትሆኑ እናደርጋለን አሉአቸው። |
15. | እነርሱም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ አስተማሩአቸው አደረጉ። ይህም ነገር በአይሁድ ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ሲወራ ይኖራል። |
16. | አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፥ |
17. | ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ የተጠራጠሩ ግን ነበሩ። |
18. | ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። 19-20 እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ። |
← Matthew (28/28) |