← Matthew (27/28) → |
1. | ሲነጋም የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሎች ሁሉ ሊገድሉት በኢየሱስ ላይ ተማከሩ፤ |
2. | አስረውም ወሰዱት፥ ለገዢው ለጴንጤናዊው ጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት። |
3. | በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፥ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ። |
4. | ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ። እነርሱ ግን። እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ። |
5. | ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ። |
6. | የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው። የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ። |
7. | ተማክረውም የሸክላ ሠሪውን መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት። |
8. | ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ። |
9. | በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው። ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥ |
10. | ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት። የሚል ተፈጸመ። |
11. | ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም። የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም። አንተ አልህ አለው። |
12. | የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም። |
13. | በዚያን ጊዜ ጲላጦስ። ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን? አለው። |
14. | ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም። |
15. | በዚያም በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው። |
16. | በዚያን ጊዜም በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው። |
17. | እንግዲህ እነርሱ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ። በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ |
18. | በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። |
19. | እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ። ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት። |
20. | የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ። |
21. | ገዢውም መልሶ። ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ እነርሱም። በርባንን አሉ። |
22. | ጲላጦስ። ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው? አላቸው፤ ሁሉም። ይሰቀል አሉ። |
23. | ገዢውም። ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አለ፤ እነርሱ ግን። ይሰቀል እያሉ ጩኸት አበዙ። |
24. | ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፥ ውኃ አንሥቶ። እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። |
25. | ሕዝቡም ሁሉ መልሰው። ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ። |
26. | በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቀል አሳልፎ ሰጠ። |
27. | በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ውስጥ ወሰዱት ጭፍራውንም ሁሉ ወደ እርሱ አከማቹ። |
28. | ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት፥ |
29. | ከእሾህም አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ፥ በቀኝ እጁም መቃ አኖሩ፥ በፊቱም ተንበርክከው። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ ዘበቱበት፤ |
30. | ተፉበትም መቃውንም ይዘው ራሱን መቱት። |
31. | ከዘበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት ሊሰቅሉትም ወሰዱት። |
32. | ሲወጡም ስምዖን የተባለው የቀሬናን ሰው አገኙ፤ እርሱንም መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። |
33. | ትርጓሜው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜም፥ |
34. | በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም። |
35. | ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ጥለው ተካፈሉ፥ |
36. | በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። |
37. | ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው የሚል የክሱን ጽሕፈት ከራሱ በላይ አኖሩ። |
38. | በዚያን ጊዜ ሁለት ወንበዶች አንዱ በቀኝ አንዱም በግራ ከእርሱ ጋር ተሰቀሉ። |
39. | የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና። |
40. | ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ አሉት። |
41. | እንዲሁም ደግሞ የካህናት አለቆች ከጻፎችና ከሽማግሎች ጋር እየዘበቱበት እንዲህ አሉ። |
42. | ሌሎችን አዳነ፥ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፥ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እናምንበታለን። |
43. | በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው። |
44. | ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዶች ደግሞ ያንኑ እያሉ ይነቅፉት ነበር። |
45. | ከስድስት ሰዓትም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። |
46. | በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም። አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው። |
47. | በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ። |
48. | ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠ፤ ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፥ በመቃም አድርጎ አጠጣው። |
49. | ሌሎቹ ግን። ተው፥ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ አሉ። |
50. | ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። |
51. | እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ |
52. | መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤ |
53. | ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። |
54. | የመቶ አለቃም ከእርሱም ጋር ኢየሱስን የሚጠብቁ መናወጡንና የሆነውን ነገር አይተው። ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ ብለው እጅግ ፈሩ። |
55. | ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፤ |
56. | ከእነርሱም መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ። |
57. | በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የተባለው ባለ ጠጋ ሰው ከአርማትያስ መጣ፥ እርሱም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ |
58. | ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። |
59. | ጲላጦስም እንዲሰጡት አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፥ |
60. | ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው፥ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ። |
61. | መግደላዊት ማርያምም ሁለተኛይቱም ማርያም በመቃብሩ አንጻር ተቀምጠው በዚያ ነበሩ። |
62. | በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ በሚሆነው ቀን፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና። |
63. | ጌታ ሆይ፥ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ። ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን። |
64. | እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም። ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት። |
65. | ጲላጦስም። ጠባቆች አሉአችሁ፤ ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው። |
66. | እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ። |
← Matthew (27/28) → |