| ← Matthew (25/28) → | 
| 1. | በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች። | 
| 2. | ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ። | 
| 3. | ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ | 
| 4. | ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ። | 
| 5. | ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። | 
| 6. | እኩል ሌሊትም ሲሆን። እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ። | 
| 7. | በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። | 
| 8. | ሰነፎቹም ልባሞቹን። መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው። | 
| 9. | ልባሞቹ ግን መልሰው። ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው። | 
| 10. | ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ። | 
| 11. | በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና። ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ። | 
| 12. | እርሱ ግን መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ። | 
| 13. | ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። | 
| 14. | ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ | 
| 15. | ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። | 
| 16. | አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ | 
| 17. | እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። | 
| 18. | አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። | 
| 19. | ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። | 
| 20. | አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ። ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። | 
| 21. | ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። | 
| 22. | ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ። | 
| 23. | ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። | 
| 24. | አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ | 
| 25. | ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። | 
| 26. | ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? | 
| 27. | ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር። | 
| 28. | ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ | 
| 29. | ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። | 
| 30. | የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። | 
| 31. | የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ | 
| 32. | አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፥ | 
| 33. | በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል። | 
| 34. | ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። | 
| 35. | ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ | 
| 36. | ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። | 
| 37. | ጻድቃንም መልሰው ይሉታል። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? | 
| 38. | እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? | 
| 39. | ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን? | 
| 40. | ንጉሡም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል። | 
| 41. | በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። | 
| 42. | ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ | 
| 43. | ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። | 
| 44. | እነርሱ ደግሞ ይመልሱና። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል። | 
| 45. | ያን ጊዜ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል። | 
| 46. | እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ። | 
| ← Matthew (25/28) → |