| ← Matthew (24/28) → | 
| 1. | ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ። | 
| 2. | እርሱ ግን መልሶ። ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። | 
| 3. | እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት። | 
| 4. | ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። | 
| 5. | ብዙዎች። እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። | 
| 6. | ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። | 
| 7. | ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ | 
| 8. | እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። | 
| 9. | በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። | 
| 10. | በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ | 
| 11. | ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ | 
| 12. | ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። | 
| 13. | እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። | 
| 14. | ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል። | 
| 15. | እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ | 
| 16. | በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ | 
| 17. | በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፥ | 
| 18. | በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። | 
| 19. | በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። | 
| 20. | ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ | 
| 21. | በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። | 
| 22. | እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ። | 
| 23. | በዚያን ጊዜ ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም። ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ | 
| 24. | ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። | 
| 25. | እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። | 
| 26. | እንግዲህ። እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ | 
| 27. | መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ | 
| 28. | በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። | 
| 29. | ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ | 
| 30. | የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ | 
| 31. | መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ። | 
| 32. | ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ | 
| 33. | እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። | 
| 34. | እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። | 
| 35. | ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። | 
| 36. | ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም። | 
| 37. | የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። | 
| 38. | በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፥ | 
| 39. | የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። | 
| 40. | በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል፤ | 
| 41. | ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች። | 
| 42. | ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። | 
| 43. | ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። | 
| 44. | ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። | 
| 45. | እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? | 
| 46. | ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤ | 
| 47. | እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። | 
| 48. | ያ ክፉ ባሪያ ግን። ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ፥ | 
| 49. | ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ | 
| 50. | የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ | 
| 51. | ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፥ እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። | 
| ← Matthew (24/28) → |