| ← Matthew (19/28) → |
| 1. | ኢየሱስም ይህን ነገር ከፈጸመ በኋላ፥ ከገሊላ ሄዶ ወደ ይሁዳ አውራጃ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ መጣ። |
| 2. | ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፥ በዚያም ፈወሳቸው። |
| 3. | ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ ቀረቡና ሲፈትኑት። ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? አሉት። |
| 4. | እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ። ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ |
| 5. | አለም። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? |
| 6. | ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። |
| 7. | እነርሱም። እንኪያስ ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ? አሉት። |
| 8. | እርሱም። ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ፤ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም። |
| 9. | እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል አላቸው። |
| 10. | ደቀ መዛሙርቱም። የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም አሉት። |
| 11. | እርሱ ግን። ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤ |
| 12. | በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፥ ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፥ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው አላቸው። |
| 13. | በዚያን ጊዜ እጁን እንዲጭንባቸውና እንዲጸልይ ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ገሠጹአቸው። |
| 14. | ነገር ግን ኢየሱስ። ሕፃናትን ተዉአቸው፥ ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉ ናትና አለ፤ |
| 15. | እጁንም ጫነባቸውና ከዚያ ሄደ። |
| 16. | እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ። መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው። |
| 17. | እርሱም። ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ አለው። |
| 18. | እርሱም። የትኞችን? አለው። ኢየሱስም። አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ |
| 19. | አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። |
| 20. | ጐበዙም። ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፥ ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው? አለው። |
| 21. | ኢየሱስም። ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው። |
| 22. | ጐበዙም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ሄደ። |
| 23. | ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ። እውነት እላችኋለሁ፥ ለባለጠጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው። |
| 24. | ዳግመኛም እላችኋለሁ፥ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል አለ። |
| 25. | ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው እጅግ ተገረሙና። እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል? አሉ። |
| 26. | ኢየሱስም እነርሱን ተመልክቶ። ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል አላቸው። |
| 27. | በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው። |
| 28. | ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ። |
| 29. | ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል። |
| 30. | ነገር ግን ብዙዎቹ ፊተኞች ኋለኞች፥ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ። |
| ← Matthew (19/28) → |