| ← Matthew (11/28) → |
| 1. | ኢየሱስም አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማዘዝ በፈጸመ ጊዜ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ከዚያ አለፈ። |
| 2. | ዮሐንስም በወህኒ ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና። |
| 3. | የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ? አለው። |
| 4. | ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ |
| 5. | ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ |
| 6. | ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው። |
| 7. | እነዚያም ሲሄዱ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ እንዲህም አለ። ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? |
| 8. | ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ፥ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ። |
| 9. | ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን። |
| 10. | እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ |
| 11. | ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። |
| 12. | ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል። |
| 13. | ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤ |
| 14. | ልትቀበሉትስ ብትወዱ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው። |
| 15. | የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። |
| 16. | ነገር ግን ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ። |
| 17. | እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም ይሉአቸዋል። |
| 18. | ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፥ እነርሱም። ጋኔን አለበት አሉት። |
| 19. | የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እነርሱም። እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል። ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች። |
| 20. | በዚያን ጊዜ የሚበዙ ተአምራት የተደረገባቸውን ከተማዎች ንስሐ ስላልገቡ ሊነቅፋቸው ጀመረ እንዲህም አለ። |
| 21. | ወዮልሽ ኮራዚ፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና። |
| 22. | ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። |
| 23. | አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና። |
| 24. | ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል። |
| 25. | በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ። አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ |
| 26. | አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። |
| 27. | ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም። |
| 28. | እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። |
| 29. | ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ |
| 30. | ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና። |
| ← Matthew (11/28) → |