| ← Matthew (10/28) → |
| 1. | አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው። |
| 2. | የአሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ይህ ነው፤ መጀመሪያው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን ወንድሙ እንድርያስም፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብም ወንድሙ ዮሐንስም፥ |
| 3. | ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥ ቶማስም ቀራጩ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ታዴዎስም የተባለው ልብድዮስ፥ |
| 4. | ቀነናዊውም ስምዖን ደግሞም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። |
| 5. | እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፥ አዘዛቸውም፥ እንዲህም አለ። በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፥ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ |
| 6. | ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ። |
| 7. | ሄዳችሁም። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ። |
| 8. | ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ። |
| 9. | ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ፥ |
| 10. | ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና። |
| 11. | በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፥ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ። |
| 12. | ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ |
| 13. | ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ። |
| 14. | ከማይቀበላችሁም ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ፥ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ። |
| 15. | እውነት እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ አገር ይቀልላቸዋል። |
| 16. | እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ። |
| 17. | ነገር ግን ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ በምኩራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤ |
| 18. | ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፥ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ። |
| 19. | አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ |
| 20. | በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና። |
| 21. | ወንድምም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ ይገድሉአቸውማል። |
| 22. | በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። |
| 23. | በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም። |
| 24. | ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፥ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም። |
| 25. | ደቀ መዝሙር እንደ መምህሩ፥ ባሪያም እንደ ጌታው መሆኑ ይበቃዋል። ባለቤቱን ብዔል ዜቡል ካሉት፥ ቤተሰዎቹንማ እንዴት አብዝተው አይሉአቸው! |
| 26. | እንግዲህ አትፍሩአቸው፤ የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና። |
| 27. | በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ። |
| 28. | ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ። |
| 29. | ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። |
| 30. | የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቈጥሮአል። |
| 31. | እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ። |
| 32. | ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ |
| 33. | በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ። |
| 34. | በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። |
| 35. | ሰውን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፥ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤ |
| 36. | ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል። |
| 37. | ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ |
| 38. | መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። |
| 39. | ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል። |
| 40. | እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። |
| 41. | ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። |
| 42. | ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም። |
| ← Matthew (10/28) → |