| ← Mark (5/16) → |
| 1. | ወደ ባሕር ማዶም ወደ ጌርጌሴኖን አገር መጡ። |
| 2. | ከታንኳይቱም በወጣ ጊዜ፥ ርኵስ መንፈስ የያዘው ሰው ከመቃብር ወጥቶ ወዲያው ተገናኘው፤ |
| 3. | እርሱም በመቃብር ይኖር ነበር፥ በሰንሰለትም ስንኳ ማንም ሊያስረው በዚያን ጊዜ አይችልም ነበር፤ |
| 4. | ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበርና ዳሩ ግን ሰንሰለቱን ይበጣጥስ እግር ብረቱንም ይሰባብር ነበር፥ ሊያሸንፈውም የሚችል አልነበረም፤ |
| 5. | ሁልጊዜም ሌሊትና ቀን በመቃብርና በተራራ ሆኖ ይጮኽ ነበር ሰውነቱንም በድንጋይ ይቧጭር ነበር። |
| 6. | ኢየሱስንም ከሩቅ ባየ ጊዜ ሮጦ ሰገደለት፥ |
| 7. | በታላቅ ድምፅም እየጮኸ። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ አለ፤ |
| 8. | አንተ ርኵስ መንፈስ፥ ከዚህ ሰው ውጣ ብሎት ነበርና። |
| 9. | ስምህ ማን ነው? ብሎ ጠየቀው። ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው አለው፥ |
| 10. | ከአገርም ውጭ እንዳይሰዳቸው አጥብቆ ለመነው። |
| 11. | በዚያም በተራራ ጥግ ብዙ የእሪያ መንጋ ይሰማራ ነበርና። |
| 12. | ወደ እሪያዎቹ እንድንገባ ስደደን ብለው ለመኑት። |
| 13. | ኢየሱስም ፈቀደላቸው። ርኵሳን መናፍስቱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ገቡ፥ ሁለት ሺህም የሚያህል መንጋ ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና በባሕር ሰጠሙ። ፍ1 ሌጌዎን ማለት ጭፍራ ማለት ነው። |
| 14. | እረኞቹም ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩ፤ ነገሩም ምን እንደ ሆነ ለማየት መጡ። |
| 15. | ወደ ኢየሱስም መጡ፥ አጋንንትም ያደሩበትን ሌጌዎንም የነበረበትን ሰው ተቀምጦ ለብሶም ልቡም ተመልሶ አዩና ፈሩ። |
| 16. | ያዩት ሰዎችም አጋንንት ላደሩበት ሰው የሆነውንና ስለ እሪያዎቹ ተረኩላቸው። |
| 17. | ከአገራቸውም እንዲሄድላቸው ይለምኑት ጀመር። |
| 18. | ወደ ታንኳይቱም በገባ ጊዜ አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው ከእርሱ ጋር እንዲኖር ለመነው። |
| 19. | ኢየሱስም አልፈቀደለትም፥ ነገር ግን። ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው አለው። |
| 20. | ሄዶም ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት አሥር ከተማ በሚባል አገር ይሰብክ ጀመር፥ ሁሉም ተደነቁ። |
| 21. | ኢየሱስም ደግሞ በታንኳይቱ ወደ ማዶ ከተሻገረ በኋላ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ በባሕርም አጠገብ ነበረ። |
| 22. | ኢያኢሮስ የተባለ ከምኵራብ አለቆች አንዱ መጣ፤ ባየውም ጊዜ በእግሩ ላይ ወደቀና። |
| 23. | ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት ብሎ አጥብቆ ለመነው። |
| 24. | ከእርሱም ጋር ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት አጋፉትም። |
| 25. | ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ |
| 26. | ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሠቃየች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም፤ |
| 27. | የኢየሱስንም ወሬ ሰምታ በስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ዳሰሰች። |
| 28. | ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ ብላለችና። |
| 29. | ወዲያውም የደምዋ ምንጭ ደረቀ ከሥቃይዋም እንደዳነች በሰውነትዋ አወቀች። |
| 30. | ወዲያውም ኢየሱስ ከእርሱ ኃይል እንደ ወጣ በገዛ ራሱ አውቆ በሕዝቡ መካከል ዘወር ብሎ። ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው? አለ። |
| 31. | ደቀ መዛሙርቱም። ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ። ማን ዳሰሰኝ ትላለህን? አሉት። |
| 32. | ይህንም ያደረገችውን ለማየት ዘወር ብሎ ይመለከት ነበር። |
| 33. | ሴቲቱ ግን የተደረገላትን ስላወቀች፥ እየፈራች እየተንቀጠቀጠችም፥ መጥታ በፊቱ ተደፋች እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። |
| 34. | እርሱም። ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ አላት። |
| 35. | እርሱም ገና ሲናገር ከምኵራብ አለቃው ቤት ዘንድ የመጡት። ልጅህ ሞታለች፤ ስለ ምን መምህሩን አሁን ታደክመዋለህ? አሉት። |
| 36. | ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ቃል አድምጦ ለምኵራቡ አለቃ። እመን ብቻ እንጂ አትፍራ አለው። |
| 37. | ከጴጥሮስም ከያዕቆብም ከያዕቆብም ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። |
| 38. | ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤትም መጥቶ ሰዎች ሲንጫጩና ሲያለቅሱ ዋይታም ሲያበዙ አየ፤ |
| 39. | ገብቶም። ስለ ምን ትንጫጫላችሁ ታለቅሳላችሁም? ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አላቸው። |
| 40. | በጣምም ሳቁበት። እርሱ ግን ሁሉን አስወጥቶ የብላቴናይቱን አባትና እናትም ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ይዞ ብላቴናይቱ ወዳለችበት ገባ። |
| 41. | የብላቴናይቱንም እጅ ይዞ። ጣሊታ ቁሚ አላት፤ ፍችውም አንቺ ብላቴና ተነሽ እልሻለሁ ነው። |
| 42. | ብላቴናይቱም የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረችና ወዲያው ቆማ ተመላለሰች። ወዲያውም ታላቅ መገረም ተገረሙ። |
| 43. | ይህንም ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አዞአቸው። የምትበላውን ስጡአት አላቸው። |
| ← Mark (5/16) → |