| ← Mark (3/16) → | 
| 1. | ደግሞም ወደ ምኵራብ ገባ፥ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር፤ | 
| 2. | ሊከሱትም፥ በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። | 
| 3. | እጁ የሰለለችውንም ሰው። ተነሥተህ ወደ መካከል ና አለው። | 
| 4. | በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን? ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል? አላቸው፤ እነርሱም ዝም አሉ። | 
| 5. | ስለ ልባቸውም ድንዛዜ አዝኖ ዙሪያውን እየተመለከተ በቍጣ አያቸው፥ ሰውየውንም። እጅህን ዘርጋ አለው። | 
| 6. | ዘረጋትም፥ እጁም ዳነች። ፈሪሳውያንም ወጥተው ወዲያው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ከሄሮድስ ወገን ጋር ተማከሩበት። | 
| 7. | ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባህር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላ የመጡም ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ | 
| 8. | እንዴት ትልቅ ነገርም እንዳደረገው ሰምተው ብዙ ሰዎች ከይሁዳ ከኢየሩሳሌምም ከኤዶምያስም ከዮርዳኖስ ማዶም ከጢሮስና ከሲዶና ምድርም ወደ እርሱ መጡ። | 
| 9. | ሰዎቹም እንዳያጋፉት ታንኳን ያቆዩለት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ | 
| 10. | ብዙ ሰዎችን አድኖ ነበርና፥ ስለዚህም ሥቃይ ያለባቸው ሁሉ እንዲዳስሱት ይወድቁበት ነበር። | 
| 11. | ርኵሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው። አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ ጮኹ። | 
| 12. | እንዳይገልጡትም በጣም አዘዛቸው። | 
| 13. | ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። | 
| 14. | ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ | 
| 15. | ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ፤ | 
| 16. | ስምዖንንም ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፤ | 
| 17. | የዘብዴዎስንም ልጅ ያዕቆብን የያዕቆብንም ወንድም ዮሐንስን ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፥ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው፤ | 
| 18. | እንድርያስንም ፊልጶስንም በርተሎሜውስንም ማቴዎስንም ቶማስንም የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብንም ታዴዎስንም ቀነናዊውንም ስምዖንን፥ | 
| 19. | አሳልፎ የሰጠውንም የአስቆሮቱን ይሁዳን። | 
| 20. | ወደ ቤትም መጡ፤ እንጀራም መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ እንደ ገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። | 
| 21. | ዘመዶቹም ሰምተው። አበደ ብለዋልና ሊይዙት ወጡ። | 
| 22. | ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጻፎችም። ብዔል ዜቡል አለበት፤ ደግሞ። በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ብለው ተናገሩ። | 
| 23. | እነርሱንም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ አላቸው። ሰይጣን ሰይጣንን ሊያወጣው እንዴት ይችላል? | 
| 24. | መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤ | 
| 25. | ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ሊቆም አይችልም። | 
| 26. | ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ከተለያየ፥ መጨረሻ ይሆንበታል እንጂ ሊቆም አይችልም። | 
| 27. | ነገር ግን አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ዕቃውን ሊበዘብዝ የሚችል የለም፥ ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል። | 
| 28. | እውነት እላችኋለሁ፥ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሁሉ የሚሳደቡትም ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤ | 
| 29. | በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም። | 
| 30. | ርኵስ መንፈስ አለበት ይሉ ነበርና። | 
| 31. | እናቱና ወንድሞቹም መጡ በውጭም ቆመው ወደ እርሱ ልከው አስጠሩት። | 
| 32. | ብዙ ሰዎችም በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና። እነሆ፥ እናትህ ወንድሞችህም በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል አሉት። | 
| 33. | መልሶም። እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነ ማን ናቸው? አላቸው። | 
| 34. | በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም ተመለከተና። እነሆ እናቴ ወንድሞቼም። | 
| 35. | የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው እኅቴም እናቴም አለ። | 
| ← Mark (3/16) → |