Malachi (3/4)  

1. እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፤ የምትወዱትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
2. ነገር ግን እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም ማን ነው?
3. እርሱም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፥ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፥ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቍርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ።
4. እግዚአብሔርም እንደ ዱሮው ዘመንና እንደ ቀደሙት ዓመታት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ቍርባን ደስ ይለዋል።
5. ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በመተተኞችና በአመንዝሮች፥ በሐሰትም በሚምሉ፥ የምንደኛውን ደመወዝ በሚከለክሉ፥ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚያስጨንቁ፥ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
6. እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ ስለዚህ የጠፋችሁ አይደላችሁም።
7. ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምር ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፥ እርስዋንም አልጠበቃችሁም። ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ግን። የምንመለሰው በምንድር ነው? ብላችኋል።
8. ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል። እናንተም። የሰረቅንህ በምንድር ነው? ብላችኋል። በአሥራትና በበኵራት ነው።
9. እናንተ፥ ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ እኔን ሰርቃችኋልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ።
10. በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ፤ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
11. ስለ እናንተ ነቀዙን እገሥጻለሁ፥ የምድራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁም ያለው ወይን ፍሬውን አያረግፍም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
12. የተድላ ምድር ትሆናላችሁና አሕዛብ ሁሉ ብፁዓን ብለው ይጠሩአችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
13. ቃላችሁ በእኔ ላይ ድፍረት ሆኖአል፥ ይላል እግዚአብሔር። እናንተ ግን። በአንተ ላይ ደፍረን የተናገርነው በምንድር ነው? ብላችኋል።
14. እናንተም። እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ ትእዛዙንስ በመጠበቅ፥ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ፊት ኀዘንተኞች ሆነን በመሄድ ምን ይረባናል?
15. አሁንም የሚታበዩትን ሰዎች ብፁዓን ብለን እንጠራቸዋለን፤ ክፉንም የሚሠሩ ጸንተዋል እግዚአብሔርንም ይፈታተናሉ፥ ያመልጣሉም ብላችኋል።
16. የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም አደመጠ፥ ሰማም፥ እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።
17. እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ ገንዘብ ይሆናሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ሰውም የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚምር፥ እንዲሁ እምራቸዋለሁ።
18. ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፥ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል ትለያላችሁ።

  Malachi (3/4)