← Luke (17/24) → |
1. | ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ። መሰናክል ግድ ሳይመጣ አይቀርም፥ ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት፤ |
2. | ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከማሰናከል ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይጠቅመው ነበር። |
3. | ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፥ ቢጸጸትም ይቅር በለው። |
4. | በቀንም ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህ በቀንም ሰባት ጊዜ። ተጸጸትሁ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ፥ ይቅር በለው። |
5. | ሐዋርያትም ጌታን። እምነት ጨምርልን አሉት። |
6. | ጌታም አለ። የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር። |
7. | ከእናንተም የሚያርስ ወይም ከብትን የሚጠብቅ ባሪያ ያለው፥ ከእርሻ ሲመለስ። ወዲያው ቅረብና በማዕድ ተቀመጥ የሚለው ማን ነው? |
8. | የምበላውን እራቴን አሰናዳልኝ፥ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፥ በኋላም አንተ ብላና ጠጣ የሚለው አይደለምን? |
9. | ያንን ባሪያ ያዘዘውን ስላደረገ ያመሰግነዋልን? |
10. | እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ። የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ። |
11. | ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። |
12. | ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት አሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ |
13. | እነርሱም እየጮኹ። ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ፥ ማረን አሉ። |
14. | አይቶም። ሂዱ፥ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው። |
15. | እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥ |
16. | እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። |
17. | ኢየሱስም መልሶ። አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? |
18. | ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ። |
19. | እርሱንም። ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። |
20. | ፈሪሳውያንም። የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ። የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ |
21. | ደግሞም። እንኋት በዚህ ወይም። እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው። |
22. | ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ። ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ልታዩ የምትመኙበት ወራት ይመጣል አታዩትምም። |
23. | እነርሱም። እነሆ በዚህ፥ ወይም። እነሆ በዚያ ይሉአችኋል፤ አትሂዱ አትከተሉአቸውም። |
24. | መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ ከአንድ አገር ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ አገር እንደሚያበራ፥ የሰው ልጅ በቀኑ እንዲህ ይሆናል። |
25. | አስቀድሞ ግን ብዙ መከራ እንዲቀበል ከዚህም ትውልድ እንዲጣል ይገባዋል። |
26. | በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። |
27. | ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር፥ የጥፋት ውኃም መጣ ሁሉንም አጠፋ። |
28. | እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ |
29. | ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ። |
30. | የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል። |
31. | በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፥ እንዲሁም በእርሻ ያለ ወደ ኋላው አይመለስ። |
32. | የሎጥን ሚስት አስቡአት። |
33. | ነፍሱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም የሚያጠፋ ሁሉ በሕይወት ይጠብቃታል። |
34. | እላችኋለሁ፥ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። |
35. | ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች ሁለተኛይቱም ትቀራለች። |
36. | ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። |
37. | መልሰውም። ጌታ ሆይ፥ ወዴት ነው? አሉት። እርሱም። ሥጋ ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ አላቸው። |
← Luke (17/24) → |