← Luke (14/24) → |
1. | በሰንበትም ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት እንጀራ ሊበላ በገባ ጊዜ እነርሱ ይጠባበቁት ነበር። |
2. | እነሆም፥ ሆዱ የተነፋ ሰው በፊቱ ነበረ። |
3. | ኢየሱስም መልሶ። በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? ብሎ ለሕግ አዋቂዎችና ለፈሪሳውያን ተናገረ። |
4. | እነርሱ ግን ዝም አሉ። ይዞም ፈወሰውና አሰናበተው። |
5. | ከእናንተ አህያው ወይስ በሬው በጕድጓድ ቢወድቅ በሰንበት ወዲያው የማያወጣው ማን ነው? አላቸው። |
6. | ስለዚህ ነገርም ሊመልሱለት አልተቻላቸውም። |
7. | የታደሙትንም የከበሬታ ስፍራ እንደ መረጡ ተመልክቶ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል። |
8. | ማንም ለሰርግ ቢጠራህ በከበሬታ ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የከበረ ተጠርቶ ይሆናልና አንተን እርሱንም የጠራ መጥቶ። |
9. | ለዚህ ስፍራ ተውለት ይልሃል፥ በዚያን ጊዜም እያፈርህ በዝቅተኛው ስፍራ ልትሆን ትጀምራለህ። |
10. | ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ፥ የጠራህ መጥቶ። ወዳጄ ሆይ፥ ወደ ላይ ውጣ እንዲልህ፥ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ ያን ጊዜም ከአንተ ጋር በተቀመጡት ሁሉ ፊት ክብር ይሆንልሃል። |
11. | ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል። |
12. | የጠራውንም ደግሞ እንዲህ አለው። ምሳ ወይም እራት ባደረግህ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ምናልባት እንዳይጠሩህ ብድራትም እንዳይመልሱልህ፥ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ባለ ጠጎች ጎረቤቶችህንም አትጥራ። |
13. | ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤ |
14. | የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና። |
15. | ከተቀመጡትም አንዱ ይህን ሰምቶ። በእግዚአብሔር መንግሥት እንጀራ የሚበላ ብፁዕ ነው አለው። |
16. | እርሱ ግን እንዲህ አለው። አንድ ሰው ታላቅ እራት አድርጎ ብዙዎችን ጠራ፤ |
17. | በእራትም ሰዓት የታደሙትን። አሁን ተዘጋጅቶአልና ኑ እንዲላቸው ባሪያውን ላከ። |
18. | ሁላቸውም በአንድነት ያመካኙ ጀመር። የፊተኛው። መሬት ገዝቼአለሁ ወጥቼም ላየው በግድ ያስፈልገኛል፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው። |
19. | ሌላውም። አምስት ጥምድ በሬዎች ገዝቼአለሁ ልፈትናቸውም እሄዳለሁ፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው። |
20. | ሌላውም። ሚስት አግብቼአለሁ ስለዚህም ልመጣ አልችልም አለው። |
21. | ባሪያውም ደርሶ ይህን ለጌታው ነገረው። በዚያን ጊዜ ባለቤቱ ተቆጥቶ ባሪያውን። ወደ ከተማ ጎዳናና ወደ ስላች ፈጥነህ ውጣ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንና ዕውሮችንም ወደዚህ አግባ አለው። |
22. | ባሪያውም። ጌታ ሆይ፥ እንዳዘዝኸኝ ተደርጎአል፥ ገናም ስፍራ አለ አለው። |
23. | ጌታውም ባሪያውን። ቤቴ እንዲሞላ ወደ መንገድና ወደ ቅጥር ውጣና ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው፤ |
24. | እላችኋለሁና፥ ከታደሙት ከእነዚያ ሰዎች አንድ ስንኳ እራቴን አይቀምስም አለው። |
25. | ብዙም ሕዝብ ከእርሱ ጋር ይሄዱ ነበር፥ ዘወር ብሎም እንዲህ አላቸው። |
26. | ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። |
27. | ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። |
28. | ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ከሳራውን የማይቈጥር ማን ነው? |
29. | ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት፥ ሊደመድመውም ቢያቅተው፥ ያዩት ሁሉ። |
30. | ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ። |
31. | ወይም ሌላውን ንጉሥ በጦርነት ሊጋጠም የሚሄድ፥ ከሁለት እልፍ ጋር የሚመጣበትን በአንድ እልፍ ሊገናኝ የሚችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የማያስብ ንጉሥ ማን ነው? |
32. | ባይሆንስ ሌላው ገና ሩቅ ሳለ መልክተኞች ልኮ ዕርቅ ይለምናል። |
33. | እንግዲህ እንደዚሁ ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። |
34. | ጨው መልካም ነው፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፈጣል? |
35. | ለምድር ቢሆን ለፍግ መቈለያም ቢሆን አይረባም፤ ወደ ውጭ ይጥሉታል። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። |
← Luke (14/24) → |