| ← Leviticus (4/27) → |
| 1. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። |
| 2. | ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም። አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ፥ |
| 3. | የተቀባውም ካህን በሕዝቡ ላይ በደል እንዲቈጠርባቸው ኃጢአት ቢሠራ፥ ስለ ሠራው ስለ ኃጢአቱ ነውር የሌለበት ወይፈን ለእግዚአብሔር ለኃጢአት መሥዋዕት ያቀርበዋል። |
| 4. | ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣዋል፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭነዋል፥ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል። |
| 5. | የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣዋል፤ |
| 6. | ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። |
| 7. | ካህኑም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለው ጣፋጭ ዕጣን በሚታጠንበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ የተረፈውንም የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። |
| 8. | ለኃጢአትም መሥዋዕት ከሚታረደው ወይፈን ስብን ሁሉ ይወስዳል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ |
| 9. | ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር፥ |
| 10. | ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ወይፈን እንደ ተወሰደው ይወስዳል። ካህኑም ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ ያቃጥለዋል። |
| 11. | የወይፈኑን ቁርበት፥ ሥጋውንም ሁሉ፥ ራሱንም፥ እግሮቹንም፥ ሆድ ዕቃውንም፥ |
| 12. | ፈርሱንም፥ ወይፈኑን ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አመድ ወደሚፈስስበት ወደ ንጹሕ ስፍራ ይወስደዋል፥ በእንጨትም ላይ በእሳት ያቃጥለዋል፤ አመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይቃጠላል። |
| 13. | የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ቢስቱ፥ ነገሩም ከጉባኤው ፊት ቢሸሸግ፥ እግዚአብሔርም። አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፉ፥ |
| 14. | እንዲህም ቢበድሉ፥ የሠሩት ኃጢአት ሲታወቅ ጉባኤው ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ወይፈንን ያቀርባሉ፤ ወደ መገናኛውም ድንኳን ፊት ያመጡታል። |
| 15. | የጉባኤውም ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ይጭናሉ፤ ወይፈኑም በእግዚአብሔር ፊት ይታረዳል። |
| 16. | የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣል፤ |
| 17. | ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመጋረጃው ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። |
| 18. | በመገናኛውም ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ባለው በዕጣን መሠዊያው ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ ደሙንም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። |
| 19. | ስቡንም ሁሉ ከእርሱ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። |
| 20. | እንዲህም በወይፈኑ ያደርጋል፤ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት በታረደው ወይፈን እንዳደረገ እንዲሁ በዚህ ያደርጋል፤ ካህኑም ስለ እነርሱ ያስተሰርያል፥ እነርሱም ይቅር ይባላሉ። |
| 21. | ወይፈኑንም ከሰፈሩ ወደ ውጭ ይወስደዋል፥ የፊተኛውንም ወይፈን እንዳቃጠለ ያቃጥለዋል፤ ይህ የማኅበሩ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። |
| 22. | አንድ መኰንንም ኃጢአትን ሲሠሩ፥ ሳያውቅም እግዚአብሔር አምላኩ። አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ሲተላለፍ፥ እንዲህም ሲበድል፥ |
| 23. | የሠራው ኃጢአት ቢታወቅ፥ ነውር የሌለበትን ተባት ፍየል ለቍርባኑ ያቀርበዋል፤ |
| 24. | በፍየሉም ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ እርሱ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። |
| 25. | ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ያደርገዋል፤ የተረፈውንም ደም ለሚቃጠል መሥዋዕት ከሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። |
| 26. | ስቡንም ሁሉ እንደ ደኅንነት መሥዋዕት ስብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ካህኑም ኃጢአቱን ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። |
| 27. | ከአገሩ ሕዝብም አንድ ሰው ኃጢአትን ሳያውቅ ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም። አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ቢተላለፍ፥ ቢበድልም፥ |
| 28. | ለእርሱም የሠራው ኃጢአት ቢታወቀው፥ ስለ ሠራው ኃጢአት ነውር የሌለባትን እንስት ፍየል ለቍርባኑ ያመጣል። |
| 29. | እጁንም በኃጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአትን መስዋዕት ያርዳል። |
| 30. | ካህኑም ከደምዋ በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። |
| 31. | ስቡም ሁሉ ከደኅንነት መሥዋዕት ላይ እንደሚወሰድ፥ ስብዋን ሁሉ ይወስዳል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ ካህኑም ስለ እርሱ ያስተሰርያል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። |
| 32. | ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት የበግ ጠቦት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለባትን እንስት ያመጣል። |
| 33. | እጁንም በኃጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፥ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ ለኃጢአት መሥዋዕት ያርዳታል። |
| 34. | ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። |
| 35. | ስቡ ሁሉ ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ጠቦት ላይ እንደሚወሰድ ስብዋን ይወስዳል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር በእሳት በተቃጠለው ቍርባን ላይ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። |
| ← Leviticus (4/27) → |