← Leviticus (3/27) → |
1. | ቍርባኑም የደኅንነት መሥዋዕት ቢሆን፥ ከላሞች መንጋ ተባት ወይም እንስት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለበትን በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። |
2. | እጁንም ለቍርባን በቀረበው ራስ ላይ ይጭናል፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። |
3. | ከደኅንነቱም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርባል፤ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ |
4. | ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር ይወስዳል። |
5. | የአሮንም ልጆች ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ያቃጥሉታል፤ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ ነው። |
6. | ለእግዚአብሔርም ለደኅንነት መሥዋዕት የሚያቀርበው ቍርባኑ ከበጎች ተባት ወይም እንስት ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ያቀርባል። |
7. | ለቍርባኑ ጠቦትን ቢያቀርብ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፤ |
8. | እጁንም ለቍርባን በቀረበው ራስ ላይ ይጭናል፥ በመገናኛው ድንኳን ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። |
9. | ከደኅንነቱም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርባል፤ ስቡን፥ እስከ ጀርባውም ድረስ የተቈረጠ ላቱን ሁሉ፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ |
10. | ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር ይወስዳል። |
11. | ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ በእሳት ላይ ለእግዚአብሔር የተደረገ የቍርባን መብል ነው። |
12. | ቍርባኑም ፍየል ቢሆን በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፤ |
13. | እጁንም በራሱ ላይ ይጭንበታል፥ በመገናኛውም ድንኳን ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። |
14. | ከእርሱም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርበዋል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ |
15. | ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር ይወስዳል። |
16. | ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ በእሳት ላይ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የተደረገ መብል ነው። ስቡ ሁሉ ለእግዚአብሔር ነው። |
17. | ስብና ደም እንዳትበሉ በምትኖሩበት ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው። |
← Leviticus (3/27) → |