Leviticus (27/27)    

1. እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2. ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ማናቸውም ሰው ሰውን ለእግዚአብሔር ሊሰጥ ቢሳል አንተ እንደምትገምተው መጠን ስለ ሰው ዋጋውን ይስጥ።
3. ለወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ እስከ ስድሳ ዓመት ድረስ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግምቱ አምሳ የብር ሰቅል ይሁን።
4. ሴትም ብትሆን ግምትዋ ሠላሳ ሰቅል ይሁን።
5. ከአምስት ዓመትም ጀምሮ እስከ ሀያ ዓመት ድረስ ግምቱ ለወንድ ሀያ ሰቅል፥ ለሴትም አሥር ሰቅል ይሁን።
6. ከአንድ ወርም እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለወንድ ግምቱ አምስት የብር ሰቅል፥ ለሴትም ግምትዋ ሦስት የብር ሰቅል ይሁን።
7. ከስድሳ ዓመትም ጀምሮ ከዚያም በላይ ወንድ ቢሆን ግምቱ አሥራ አምስት ሰቅል፥ ለሴትም አሥር ሰቅል ይሁን።
8. ለግምቱም የሚከፍለውን ቢያጣ ግን በካህኑ ፊት ይቁም፥ ካህኑም የተሳለውን ሰው ይገምተው፤ ካህኑም የተሳለው ሰው እንደሚችል መጠን ይገምተው።
9. ለእግዚአብሔርም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው እንስሳ ቢሆን፥ ሰው ከእነዚህ ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።
10. መልካሙን በክፉ፥ ክፉውንም በመልካም አይለውጥ፤ እንስሳንም በእንስሳ ቢለውጥ እርሱና ልዋጩ የተቀደሱ ይሆናሉ።
11. እንስሳው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት መሆን የማይገባው ርኩስ ቢሆን፥ እንስሳውን በካህኑ ፊት ያኑረው።
12. መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን ካህኑ ይገምተው፤ ካህኑም እነሚገምተው መጠን እንዲሁ ይሁን።
13. ይቤዠውም ዘንድ ቢወድድ ከግምቱ በላይ አምስተኛ ይጨምር።
14. ሰውም ለእግዚአብሔር ቅዱስ ይሆን ዘንድ ቤቱን ቢቀድስ፥ ካህኑ መልካም ወይም ክፉ እንደ ሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይቆማል።
15. የቀደሰውም ሰው ቤቱን ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ ከግምቱ ገንዘብ በላይ አምስተኛ ይጨምር፤ ቤቱም ለእርሱ ይሆናል።
16. ሰውም ከርስቱ እርሻ ለእግዚአብሔር ቢቀድስ፥ እንደ መዘራቱ መጠን ይገመት፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ የሚዘራበት እርሻ አምሳ የብር ሰቅል ይገመታል።
17. እርሻውንም ከኢዮቤልዩ ዓመት ጀምሮ ቢቀድስ፥ እንደ ግምቱ መጠን ይቆማል።
18. እርሻውንም ከኢዮቤልዩ ዓመት በኋላ ቢቀድስ፥ ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ እንደ ቀሩት ዓመታት ገንዘቡን ይቈጥርለታል፤ ከግምቱም ይጐድላል።
19. እርሻውንም የቀደሰ ሰው ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ፥ ከግምቱ ገንዘብ በላይ አምስተኛ ይጨምር፤ ለእርሱም ይሆናል።
20. እርሻውንም ባይቤዠው፥ ወይም ለሌላ ሰው ቢሸጥ፥ እንደገና ይቤዠው ዘንድ አይቻለውም።
21. እርሻው ግን በኢዮቤልዩ ሲወጣ እንደ እርም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ እርሻ ይሆናል፤ ርስቱ ለካህኑ ይሆናል።
22. ከርስቱ እርሻ ያልሆነውን የገዛውን እርሻ ለእግዚአብሔር ቢቀድስ፥
23. ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የግምቱን ዋጋ ይቈጥርለታል፤ በዚያም ቀን ግምቱን እንደ ተቀደሰ ነገር ለእግዚአብሔር ይሰጣል።
24. በኢዮቤልዩ ዓመት እርሻው የምድሪቱ ባለ ርስት ወደ ነበረው ወደ ሸጠው ሰው ይመለሳል።
25. ግምቱም ሁሉ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ይሆናል፤ ሰቅሉ ሀያ አቦሊ ይሆናል።
26. ለእግዚአብሔር ግን የሚቀርበውን የእንስሳ በኵራት ማንም ይቀድሰው ዘንድ አይቻለውም፤ በሬ ቢሆን ወይም በግ ለእግዚአብሔር ነው።
27. የረከሰም እንስሳ ቢሆን እንደ ግምቱ ይቤዠው፥ በእርሱም የዋጋውን አምስተኛ ይጨምርበታል፤ ባይቤዠውም እንደ ግምቱ ይሸጣል።
28. ለእግዚአብሔርም የተለየ እርም የሆነ ነገር ሁሉ፥ ሰው ቢሆን ወይም እንስሳ ወይም የርስቱ እርሻ ቢሆን፥ አይሸጥም፥ አይቤዥም፤ እርም የሆነ ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ቅዱሳን ነው።
29. ከሰዎችም እርም የሆነ ሁሉ አይቤዥም፤ ፈጽሞ ይገደላል።
30. የምድርም አሥራት፥ ወይም የምድር ዘር ወይም የዛፍ ፍሬ ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ነው፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው።
31. ሰውም አሥራቱን ሊቤዥ ቢወድድ፥ አምስተኛ ይጨምርበታል።
32. ከበሬም ሁሉ ከአሥር አንድ፥ ከእረኛውም በትር በታች ከሚያልፍ በግና ፍየል ሁሉ ከአሥር አንድ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል።
33. መልካም ወይም ክፉ እንዲሆን አይመርምር፥ አይለውጥም፤ ቢለውጠውም እርሱና ልዋጩ የተቀደሱ ይሆናሉ፤ አይቤዠውም።
34. እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለእስራኤል ልጆች ሙሴን ያዘዘው ትእዛዛት እነዚህ ናቸው።

  Leviticus (27/27)