← Leviticus (26/27) → |
1. | እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለእናንተ ጣዖት አታድርጉ፥ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ። |
2. | ሰንበታቴን ጠብቁ፥ መቅደሴንም ፍሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። |
3. | በሥርዓቴ ብትሄዱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉትም፥ |
4. | ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፥ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች፥ የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። |
5. | የእህሉም ማበራየት በእናንተ ዘንድ እስከ ወይኑ መቍረጥ ይደርሳል፥ የወይኑም መቍረጥ እስከ እህሉ መዝራት ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፥ በምድራችሁም ላይ በጸጥታ ትኖራላችሁ። |
6. | በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ፥ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። |
7. | ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፥ በፊታችሁም በሰይፍ ይወድቃሉ። |
8. | ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፥ መቶውም አሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። |
9. | ፊቴም ወደ እናንተ ይሆናል፥ እንድታፈሩም አደርጋችኋለሁ፥ አበዛችሁማለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። |
10. | ብዙ ጊዜ የተቀመጠውንም አሮጌውን እህል ትበላላችሁ፤ ከአዲሱም በፊት አሮጌውን ታወጣላችሁ። |
11. | ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። |
12. | በመካከላችሁም እሄዳለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፥ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ። |
13. | ባሪያዎች እዳትሆኑአቸው ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነታችሁን ቀንበር ሰብሬአለሁ፤ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ። |
14. | ነገር ግን ባትሰሙኝ፥ እነዚህንም ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ |
15. | ሥርዓቴንም ብትንቁ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ እንዳታደርጉ፥ ቃል ኪዳኔንም እንድታፈርሱ ነፍሳችሁ ፍርዴን ብትጸየፍ፥ |
16. | እኔም እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሃትን፥ ክሳትንም፥ ዓይናችሁንም የሚያፈዝዝ፥ ሰውነታችሁንም የሚያማስን ትኩሳት አወርድባችኋለሁ፤ ዘራችሁንም በከንቱ ትዘራላችሁ፥ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና። |
17. | ፊቴንም አከብድባችኋለሁ፥ በጠላቶቻችሁም ፊት ትወድቃላችሁ፤ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። |
18. | እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኃጢአታችሁ በቅጣታችሁ ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ። |
19. | የኃይላችሁንም ትዕቢት እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። |
20. | ጕልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም እህልዋን አትሰጥም፥ የምድርም ዛፎች ፍሬአቸውን አይሰጡም። |
21. | በእንቢተኝነትም ብትሄዱብኝ ባትሰሙኝም፥ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን በመቅሠፍት ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ። |
22. | በመካከላችሁም የምድርን አራዊት እሰድዳለሁ፤ ልጆቻችሁንም ይነጥቃሉ፥ እንስሶቻችሁንም ያጠፋሉ፥ እናንተንም ያሳንሳሉ፤ መንገዶቻችሁም በረሃ ይሆናሉ። |
23. | እስከዚህም ድረስ ባትቀጡ፥ በእንቢተኝነትም ብትሄዱ፥ |
24. | እኔ ደግሞ በእንቢተኝነት እሄድባችኋለሁ፤ ስለ ኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ። |
25. | የቃል ኪዳኔንም በቀል ይበቀልባችሁ ዘንድ ሰይፍ አመጣባችኋለሁ፤ ወደ ከተማችሁም ትሰበሰባላችሁ፥ ቸነፈርንም እሰድድባችኋለሁ፤ በጠላትም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ። |
26. | የእህላችሁንም ድጋፍ በሰበርሁ ጊዜ፥ አሥር ሴቶች እንጀራቸውን በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፥ በሚዛንም መዝነው እንጀራችሁን ይመልሱላችኋል፤ በበላችሁም ጊዜ አትጠግቡም። |
27. | እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ በእንቢተኝነትም ብትሄዱብኝ፥ |
28. | እኔ ደግሞ በቍጣ እሄድባችኋለሁ፤ ስለ ኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። |
29. | የወንዶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ፤ የሴቶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ። |
30. | የኮረብታ መስገጃዎቻችሁንም አፈርሳለሁ፥ የፀሐይ ምስሎቻችሁንም አጠፋለሁ፥ ሬሳችሁንም በጣዖቶቻችሁ ሬሳዎች ላይ እጥላለሁ፤ ነፍሴም ትጸየፋችኋለች። |
31. | ከተሞቻችሁንም ባድማ አደርጋለሁ፥ መቅደሶቻችሁንም አፈርሳለሁ፥ መልካሙንም መዓዛችሁን አላሸትትም። |
32. | ምድሪቱንም የተፈታች አደርጋለሁ፤ የሚቀመጡባት ጠላቶቻችሁም በእርስዋ የተነሣ ይደነቃሉ። |
33. | እናንተንም ከአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፥ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፥ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ። |
34. | በዚያም በተፈታችበት ዘመን ሁሉ እናንተም በጠላቶቻችሁ ምድር ሳላችሁ፥ ምድሪቱ ሰንበት በማድረግዋ ትደሰታለች፤ በዚያም ጊዜ ምድሪቱ ታርፋለች፥ ሰንበትንም በማድረግዋ ትደሰታለች። |
35. | እናንተ ተቀምጣችሁባት በነበረ ጊዜ በሰንበቶቻችሁ አላረፈችም ነበርና በተፈታችበት ዘመን ሁሉ ታርፋለች። |
36. | በጠላቶቻቸውም ምድሮች ሳሉ ከእናንተ ተለይተው በቀሩት ላይ በልባቸው ድንጋጤን እሰድድባቸዋለሁ፤ በነፋስም የምትንቀሳቀስ የቅጠል ድምፅ ታሸብራቸዋለች፤ ከሰይፍ እንደሚሸሹ ይሸሻሉ፤ ማንም ሳያሳድዳቸው ይወድቃሉ። |
37. | ማንም ሳያሳድዳቸው ከሰይፍ እንዲሸሹ እርስ በርሳቸው ይሰነካከላሉ፤ እናንተም በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም። |
38. | በአሕዛብም መካከል ታልቃላችሁ፥ የጠላቶቻችሁም ምድር ትውጣችኋለች። |
39. | ከእናንተም ተለይተው የቀሩት በጠላቶቻቸው ምድር ላይ በኃጢአታቸው ይከሳሉ፤ በአባቶቻቸውም ኃጢአት ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይከሳሉ። |
40. | በእኔም ላይ በእንቢተኝነት ስለ ሄዱብኝ የበደሉኝን በደል፥ ኃጢአታቸውንም፥ የአባቶቻቸውንም ኃጢአት ይናዘዛሉ። |
41. | እኔም ደግሞ በእንቢተኝነት ሄድሁባቸው፤ ወደ ጠላቶቻቸውም ምድር አገባኋቸው፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድ፥ የኃጢአታቸውንም ቅጣት ቢቀበሉ፥ |
42. | እኔ ለያዕቆብ የማልሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ደግሞ ለይስሐቅና ለአብርሃም የማልሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ምድሪቱንም አስባለሁ። |
43. | ምድርም ከእነርሱ መጥፋት የተነሣ ባዶ ትቀራለች፤ እነርሱም ሳይኖሩ በተፈታችበት ዘመን ሰንበት በማድረግዋ ትደሰታለች፤ ፍርዴንም ስለ ናቁ፥ ነፍሳቸውም ሥርዓቴን ስለ ተጸየፈች የኃጢአታቸውን ቅጣት ይሸከማሉ። |
44. | ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝኛ እነርሱ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ፥ እስካጠፋቸው ድረስ ከእነርሱም ጋር ያለኝን ቃል ኪዳን እስካፈርስ ድረስ አልጥላቸውም አልጸየፋቸውምም። |
45. | እኔ አምላካቸው እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸውን የአባቶቻቸውን ቃል ኪዳን ስለ እነርሱ አስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። |
46. | እግዚአብሔርም በእርሱና በእስራኤል ልጆች መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ እጅ ያደረጋቸው ሥርዓቶችና ፍርዶች ሕግጋትም እነዚህ ናቸው። |
← Leviticus (26/27) → |