← Leviticus (25/27) → |
1. | እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
2. | ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር ሰንበት ታድርግ። |
3. | ስድስት ዓመት እርሻህን ዝራ፥ ስድስት ዓመትም ወይንህን ቍረጥ ፍሬዋንም አግባ። |
4. | በሰባተኛው ዓመት ግን ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት፥ ለእግዚአብሔር ሰንበት፥ ትሁን፤ እርሻህን አትዝራ፥ ወይንህንም አትቍረጥ። |
5. | የምድራችሁን የገቦ አትጨደው፥ ያልተቈረጠውንም የወይንህን ፍሬ አታከማች፤ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ዓመት ይሁን። |
6. | የምድርም ሰንበት ለአንተ፥ ለወንድ ባሪያህም፥ ለሴት ባሪያህም፥ ለምንደኛውም፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ይሁን። |
7. | ለእንስሶችህም፥ በምድርህም ላሉት አራዊት ፍሬዋ ሁሉ መኖ ይሁን። |
8. | ሰባት ጊዜ ሰባት አድርገህ የዓመታትን ሰንበት ሰባት ቍጠር፤ የሰባት ዓመታትም ሰንበት ዘመን አርባ ዘጠኝ ዓመት ትቈጥራለህ። |
9. | ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን በቀንደ መለከት ታውጃለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ በቀንደ መለከት ታውጃላችሁ። |
10. | አምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፥ በምድሪቱም ለሚኖሩባት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእናንተ ኢዮቤልዩ ነው፤ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለስ። |
11. | ያ አምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆናል፤ በእርሱም አትዝሩ፥ የገቦውንም አትጨዱ፥ የወይኑንም ፍሬ አታከማቹ። |
12. | ኢዮቤልዩ ነውና የተቀደሰ ይሁንላችሁ፤ በሜዳ ላይ የበቀለውን ብሉ። |
13. | በዚች በኢዮቤልዩ ዓመት ሰው ሁሉ ወደ ርስቱ ይመለሳል። |
14. | ለባልንጀራህም አንዳች ብትሸጥለት፥ ወይም ከባልንጀራህ እጅ ብትገዛ፥ ሰው ባልንጀራውን አያታልል። |
15. | ከኢዮቤልዩ በኋላ እንደ ዓመታቱ ቍጥር ከባልንጀራህ ትገዛለህ፤ እርሱም እንደ መከሩ ዓመታት ቍጥር ይሸጥልሃል። |
16. | እንደ ዓመታቱ ብዛት ዋጋውን ታበዛለህ፥ እንደ ዓመታቱም ማነስ ዋጋውን ታሳንሳለህ፤ እንደ መከሩ ቍጥር ይሸጥልሃል። |
17. | እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰው ባልንጀራውን አያታልል፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። |
18. | ሥርዓቴንም አድርጉ፥ ፍርዶቼንም ጠብቁ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ። |
19. | ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፥ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርስዋም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ። |
20. | እናንተም። ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን? ብትሉ፥ |
21. | እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በላያችሁ አዝዛለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች። |
22. | በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ከአሮጌውም እህል ትበላላችሁ፤ ፍሬዋ እስኪገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ከአሮጌው እህል ትበላላችሁ። |
23. | ምድርም ለእኔ ናትና፥ እናንተም ከእኔ ጋር እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድርን ለዘላለም አትሽጡ። |
24. | በርስታችሁም ምድር ሁሉ መቤዠትን ለምድሪቱ አድርጉ። |
25. | ወንድምህም ቢደኸይ ከርስቱም ቢሸጥ፥ ለእርሱ የቀረበ ዘመዱ መጥቶ ወንድሙ የሸጠውን ይቤዠዋል። |
26. | የሚቤዠውም ሰው ቢያጣ፥ እርሱም እጁ ቢረጥብ፥ ለመቤዠትም የሚበቃ ቢያገኝ፥ |
27. | የሽያጩን ዘመን ቈጥሮ የቀረውን ወደ ገዛው ሰው ይመልስ፤ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ። |
28. | ለራሱም ዕዳውን መክፈል ባይችል፥ ሽያጩ በገዛው ሰው እጅ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቀመጥ፤ በኢዮቤልዩም ዓመት ይውጣ፥ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ። |
29. | ሰውም ቅጥር ባለበት ከተማ መኖሪያ ቤትን ቢሸጥ፥ ከተሸጠ በኋላ አንድ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ለመቤዠት ይችላል፤ ለአንድ ሙሉ ዓመት መቤዠት ይችላል። |
30. | አንድ ዓመትም እስኪጨረስ ባይቤዠው፥ ቅጥር ባለበት ከተማ የሚሆን ቤት ለገዛው ለልጅ ልጁ ለዘላለም ይጸናለታል፤ በኢዮቤልዩም ከእርሱ አይወጣም። |
31. | ቅጥር በሌለበት መንደር ያሉ ቤቶች ግን እንደ እርሻ ይቈጠራሉ፤ ይቤዣሉ፥ በኢዮቤልዩም ይወጣሉ። |
32. | በእነርሱ ከተማ ያለ የሌዋውያን ቤት ግን ሌዋውያን ለዘላለም መቤዠት ይችላሉ። |
33. | ማናቸውም ሰው ከሌዋውያን ቢገዛ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል የሌዋውያን ከተማ ቤቶች ርስቶቻቸው ናቸውና በርስቱ ከተማ ያለ የተሸጠው ቤት በኢዮቤልዩ ይመለሳል። |
34. | በከተማቸውም ዙሪያ ያለችው መሰምርያ የዘላለም ርስታቸው ናትና አትሸጥም። |
35. | ወንድምህ ቢደኸይ እጁም በአንተ ዘንድ ቢደክም፥ አጽናው፤ እንደ እንግዳና እንደ መጻተኛም ከአንተ ጋር ይኑር። |
36. | ወንድምህ ከአንተ ጋር ይኖር ዘንድ ከእርሱ ምንም ወለድ ወይም ትርፍ አትውሰድ፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። |
37. | ብርህን በወለድ አታበድረው፤ መኖህንም በትርፍ አትስጠው። |
38. | የከነዓንን ምድር እሰጣችሁ ዘንድ፥ አምላክም እሆናችሁ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። |
39. | ወንድምህም ቢደኸይ ራሱንም ለአንተ ቢሸጥ፥ እንደ ባሪያ አድርገህ አትግዛው። |
40. | እንደ ምንደኛና እንደ መጻተኛ ከአንተ ጋር ይሁን፤ እስከ ኢዮቤልዩም ዓመት ያገልግልህ። |
41. | በዚያን ጊዜም እርሱ ከልጆቹ ጋር ከአንተ ይውጣ፥ ወደ ወገኖቹም ወደ አባቱም ርስት ይመለስ። |
42. | ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸውና እንደ ባሪያዎች አይሸጡ። |
43. | በጽኑ እጅ አትግዛው፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። |
44. | ወንድ ባሪያና ሴት ባሪያ መግዛት ብትፈልግ ግን በዙሪያችሁ ካሉት ከእነርሱ ከአሕዛብ ወንድና ሴት ባሪያዎችን ግዙ። |
45. | ደግሞም በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት መጻተኞች፥ በምድራችሁም ውስጥ ከወለዱአቸው በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት ከዘራቸው ውስጥ ባሪያዎችን ግዙ፤ ርስትም ይሁኑላችሁ። |
46. | ከእናንተም በኋላ ልጆቻችሁ ይወርሱአቸው ዘንድ ተዉአቸው፤ ከእነርሱም ባሪያዎችን ለዘላለም ትወስዳላችሁ፤ ነገር ግን የእስራኤልን ልጆች ወንድሞቻችሁን በጽኑ እጅ አትግዙአቸው። |
47. | በአንተም ዘንድ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆን፥ ወንድምህም በእርሱ አጠገብ ቢደኸይ፥ ራሱንም ለመጻተኛው ወይም ለእንግዳው ወይም ለወገኖቹ ዘር ቢሸጥ፥ |
48. | ከተሸጠ በኋላ መቤዠት ይችላል፤ ከወንድሞቹ አንዱ ይቤዠው፤ |
49. | ወይም አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ይቤዠው፤ ወይም ከወገኑ ለእርሱ የቀረበ ዘመድ ይቤዠው፤ ወይም እርሱ እጁ ቢረጥብ ራሱን ይቤዠው። |
50. | ከገዛውም ሰው ጋር ከገዛበት ዓመት ጀምሮ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቍጠር፤ የሽያጩም ብር እንደ ዓመታቱ ቍጥር ይሁን፤ እንደ ምንደኛውም ዘመን ከእርሱ ጋር ይሁን። |
51. | ብዙ ዓመታትም ቢቀሩ እንደ እነርሱ ቍጥር ከሽያጩ ብር የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። |
52. | እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ጥቂቶች ዓመታት ቢቀሩ ከእርሱ ጋር ይቈጥራል፤ እንደ ዓመታቱም መጠንየመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። |
53. | በየዓመቱ እንደ ምንደኛ ከእርሱ ጋር ይኑር፤ በፊትህ በጽኑ እጅ አይግዛው። |
54. | በዚህ ዘመን ሁሉ ግን ባይቤዥ በኢዮቤልዩ ዓመት እርሱ ከልጆቹ ጋር ይውጣ። |
55. | የእስራኤል ልጆች ለእኔ ባሪያዎች ናቸውና፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። |
← Leviticus (25/27) → |