| ← Leviticus (24/27) → |
| 1. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 2. | መብራቱን ሁልጊዜ እንድታበራበት ለመብራት ጥሩ ተወቅጦ የተጠለለ የወይራ ዘይት ያመጡልህ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። |
| 3. | በምስክሩ መጋረጃ ውጭ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አሮን ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ያሰናዳው፤ ለዘላለም ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ይሁን። |
| 4. | በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ መቅረዝ ላይ መብራቶቹን ሁልጊዜ ያሰናዳቸው። |
| 5. | መልካሙንም ዱቄት ወስደህ አሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ በአንድ ኅብስት ውስጥ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ ይሁን። |
| 6. | እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ተርታ አድርገህ በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ ገበታ ላይ አኑራቸው። |
| 7. | ለእግዚአብሔርም ለእሳት ቍርባን በእንጀራው ላይ ለመታሰቢያ ይሆን ዘንድ በሁለቱ ተርታ ላይ ጥሩ ዕጣን አድርግ። |
| 8. | በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ በሰንበት ቀን ሁሉ በተርታ ያድርገው፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ቃል ኪዳን ነው። |
| 9. | ለአሮንና ለልጆቹም ይሁን፤ በእሳት ከተደረገው ከእግዚአብሔር ቍርባን በዘላለም ሥርዓት ለእርሱ ቅዱስ ቅዱሳን ነውና በተቀደሰ ስፍራ ይብሉት። |
| 10. | አባቱ ግብፃዊ የነበረ የእስራኤላዊት ልጅ በእስራኤል ልጆች መካከል ወጣ፤ የእስራኤላዊቱ ልጅና አንድ እስራኤላዊ በሰፈር ውስጥ ተጣሉ፤ |
| 11. | የእስራኤላዊቱም ልጅ የእግዚአብሔርን ስም ሰደበ፥ አቃለለውም፤ ወደ ሙሴም አመጡት። እናቱም ከዳን ነገድ የደብራይ ልጅ ነበረች፥ ስምዋም ሰሎሚት ነበረ። |
| 12. | ከእግዚአብሔርም አፍ ስለ እርሱ ፍርድ እስኪወጣላቸው ድረስ በግዞት አኖሩት። |
| 13. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 14. | ተሳዳቢውን ከስፈሩ ወደ ውጭ አውጣው፤ የሰሙትም ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገረው። |
| 15. | ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ትነግራለህ። ማናቸውም ሰው አምላኩን ቢሰድብ ኃጢአቱን ይሸከማል። |
| 16. | የእግዚአብሔርንም ስም የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛ ወይም የአገር ልጅ ቢሆን፥ የእግዚአብሔርን ስም በሰደበ ጊዜ ይገደል። |
| 17. | ሰውንም እስኪሞት ድረስ የሚመታ ፈጽሞ ይገደል። |
| 18. | እንስሳንም እስኪሞት ድረስ የሚመታ ሕይወት በሕይወት ፋንታ ካሣውን ይክፈል። |
| 19. | ሰውም ባልንጀራውን ቢጐዳ፥ እርሱ እንዳደረገ እንዲሁ ይደረግበት። |
| 20. | ስብራት በስብራት ፋንታ፥ ዓይን በዓይን ፋንታ፥ ጥርስ በጥርስ ፋንታ፥ ሰውን እንደ ጐዳ እንዲሁ ይደረግበት። |
| 21. | እንስሳውንም የሚገድል ካሣ ይተካ፤ ሰውንም የሚገድል ይገደል። |
| 22. | እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለመጻተኛና ለአገር ልጅ አንድ ዓይነት ሕግ ይሁንላችሁ። |
| 23. | ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገራቸው፤ ተሳዳቢውንም ከሰፈሩ ወደ ውጭ አወጡት፥ በድንጋይም ወገሩት። የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። |
| ← Leviticus (24/27) → |