| ← Leviticus (23/27) → |
| 1. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 2. | ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። የተቀደሰ ጉባኤ ብላችሁ የምታውጁአቸው በዓላቶቼ፥ የእግዚአብሔር በዓላት፥ እነዚህ ናቸው። |
| 3. | ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ በሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንበታል፤ ምንም ሥራ አትሠሩም፤ በምትኖሩበት ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። |
| 4. | እነዚህ የእግዚአብሔር በዓላት፥ በየዘመናቸው የምታውጁአቸው፥ የተቀደሰ ጉባኤ ናቸው። |
| 5. | በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ሲመሽ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው። |
| 6. | በዚህም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን ለእግዚአብሔር የቂጣ በዓል ነው፤ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ብሉ። |
| 7. | በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። |
| 8. | ሰባት ቀንም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አቅርቡ፤ በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነው፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። |
| 9. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 10. | ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ መከሩንም ባጨዳችሁ ጊዜ፥ የእናንተን መከር በኵራት ነዶ ወደ ካህኑ አምጡ፤ |
| 11. | እርሱም ነዶውን በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምርላችሁ ይወዝውዘው፤ በማግስቱ ከሰንበት በኋላ ካህኑ ይወዝውዘው። |
| 12. | ነዶውንም በወዘወዛችሁበት ቀን ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ። |
| 13. | የእህልም ቍርባን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለእሳት ቍርባን ይሁን፤ የመጠጡም ቍርባን የወይን ጠጅ የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ ይሁን። |
| 14. | እንጀራውንም፥ የተጠበሰውንም እሸት፥ ለምለሙንም እሸት የአምላካችሁን ቍርባን እስከምታቀርቡበት እስከዚህ ቀን ድረስ አትብሉ። ይህ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው። |
| 15. | የወዘወዛችሁትን ነዶ ከምታመጡበት ቀን በኋላ ከሰንበት ማግስት ፍጹም ሰባት ጊዜ ሰባት ቀን ቍጠሩ፤ |
| 16. | እስከ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቍጠሩ፤ አዲሱንም የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ። |
| 17. | ከየማደሪያችሁ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ ከሆነ መልካም ዱቄት የተሠራ ሁለት የመወዝወዝ እንጀራ ታመጣላችሁ፤ ለእግዚአብሔር ለበኵራት ቍርባን እንዲሆን በእርሾ ይጋገራል። |
| 18. | ከእንጀራውም ጋር ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ሰባት ጠቦቶች፥ አንድ ወይፈንም፥ ሁለትም አውራ በጎች ታቀርባላችሁ፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ይሁኑ፤ ከእህልም ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ጋር ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የእሳት ቍርባን ይሁኑ። |
| 19. | አንድም አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ለደኅንነት መሥዋዕት አቅርቡ። |
| 20. | ካህኑም ከበኵራቱ እንጀራ ከሁለቱም ጠቦቶች ጋር በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ይወዘውዛቸዋል፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ፈንታ ነው፤ ለካህኑ ይሁን። |
| 21. | በዚያም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችሁ ዘንድ ታውጃላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው። |
| 22. | የምድራችሁንም መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር ፈጽማችሁ አትጨዱ፥ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተዉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። |
| 23. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 24. | ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ። |
| 25. | የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት ቍርባንን አቅርቡ። |
| 26. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 27. | በዚህ በሰባተኛው ወር አሥረኛው ቀን የማስተስረያ ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁን አስጨንቋት፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት ቍርባንን አቅርቡ። |
| 28. | በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት ማስተስረያ ይሆንላችሁ ዘንድ የማስተስረያ ቀን ነውና በዚያ ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩ። |
| 29. | በዚያም ቀን የማይዋረድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። |
| 30. | በዚያም ቀን ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል አጠፋዋለሁ። |
| 31. | ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው። |
| 32. | የዕረፍት ሰንበት ይሁንላችሁ፥ ሰውነታችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን በማታ ጊዜ፥ ከማታ ጀምራችሁ እስከ ማታ ድረስ፥ ሰንበታችሁን አድርጉ። |
| 33. | እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 34. | ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። በዚህ በሰባተኛው ወር ከአሥራ አምስተኛው ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይሆናል። |
| 35. | በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁን፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት። |
| 36. | ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባንን አቅርቡ፤ በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፥ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠለውን ቍርባን አቅርቡ፤ ዋና ጉባኤ ነው፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት። |
| 37. | የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህሉንም ቍርባን፥ መሥዋዕቱንም፥ የመጠጡንም ቍርባን፥ በየቀኑ የእሳት ቍርባን ወደ እግዚአብሔር ታቀርቡባቸው ዘንድ የተቀደሱ ጉባኤዎች እንዲሆኑ የምታውጁአቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። |
| 38. | እነዚህም ከእግዚአብሔር ሰንበታት ሌላ፥ ለእግዚአብሔርም ከምትሰጡት ከስጦታችሁ ሌላ፥ ከስእለታችሁም ሁሉ ሌላ፥ በፈቃዳችሁም ከምታቀርቡአቸው ሁሉ ሌላ ናቸው። |
| 39. | ከሰባተኛውም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን የምድሩን ፍሬ ካከማቻችሁ በኋላ፥ የእግዚአብሔርን በዓል ሰባት ቀን ጠብቁ፤ በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት ይሁን፥ በስምንተኛውም ቀን ዕረፍት ይሁን። |
| 40. | በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፥ የሰሌን ቅርንጫፍ፥ የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ፥ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ። |
| 41. | ይህንንም በዓል በየዓመቱ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር አድርጉ፤ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው፤ በሰባተኛው ወር ትጠብቁታላችሁ። |
| 43. | ሰባት ቀን በዳሶች ውስጥ ትቀመጣላችሁ፤ ከግብፅ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በዳስ ውስጥ እንዳስቀመጥኋቸው የልጅ ልጆቻችሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእስራኤል ያሉት የአገር ልጆች ሁሉ በዳስ ውስጥ ይቀመጡ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። |
| 44. | ሙሴም የእግዚአብሔርን በዓላት ለእስራኤል ልጆች ተናገረ። |
| ← Leviticus (23/27) → |