← Leviticus (21/27) → |
1. | እግዚአብሔርም ሙሴን። ለካህናቱ ለአሮን ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው አለው። ማንም ሰው ከሕዝቡ ስለ ሞተው፥ |
2. | ከሚቀርበው ዘመዱ፥ ከእናቱ፥ ወይም ከአባቱ፥ ወይም ከወንድ ልጁ፥ ወይም ከሴት ልጁ፥ ወይም ከወንድሙ በቀር አይርከስ። |
3. | ወይም የቀረበችው ያልተጋባች ድንግል እኅቱ በእርስዋ ይርከስ። |
4. | የሕዝቡ አለቃ ራሱን ያጐሰቍል ዘንድ አይርከስ። |
5. | ራሳቸውን አይላጩ፥ ጢማቸውንም አይላጩ፥ ሥጋቸውንም አይንጩ። |
6. | ለአምላካቸው ቅዱሳን ይሁኑ፥ የአምላካቸውንም ስም አያጐስቍሉ፤ የእግዚአብሔርን የእሳት ቍርባንና የአምላካቸውን እንጀራ ያቀርባሉና ቅዱሳን ይሁኑ። |
7. | ለአምላኩ የተቀደሰ ነውና ጋለሞታን ሴት ወይም የረከሰችውን አያግባ፤ ወይም ከባልዋ የተፈታችውን አያግባ። |
8. | የአምላክህን እንጀራ ያቀርባልና ስለዚህ ትቀድሰዋለህ፤ እኔም የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና እርሱ ቅዱስ ይሁንልህ። |
9. | የካህንም ልጅ ራስዋን በግልሙትና ብታረክስ አባትዋን ታረክሰዋለች፤ በእሳት ትቃጠል። |
10. | በራሱም ላይ የቅባት ዘይት የፈሰሰበት፥ የክህነትም ልብስ ይለብስ ዘንድ የተቀደሰ ከወንድሞቹ የበለጠው ካህን ራሱን አይግለጥ ልብሱንም አይቅደድ። |
11. | ወደ በድንም ሁሉ አይግባ፥ በአባቱም ወይም በእናቱ አይርከስ። |
12. | የአምላኩም ቅባት ዘይት ቅዱስነት በላዩ ነውና ከመቅደስ አይውጣ፥ የአምላኩንም መቅደስ አያርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። |
13. | እርሱም ሚስትን በድንግልናዋ ያግባ። |
14. | ባልዋ የሞተባትን፥ ወይም የተፋታችውን፥ ወይም ጋለሞታይቱን አያግባ፤ ነገር ግን ከሕዝቡ ድንግሊቱን ያግባ። |
15. | እኔም የምቀድሰው እግዚአብሔር ነኝና በሕዝቡ መካከል ዘሩን አያጐስቍል። |
16. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
17. | ለአሮን እንዲህ ብለህ ንገረው። ከዘርህ በትውልዳቸው ነውር ያለበት ሰው ሁሉ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ። |
18. | ዕውር፥ ወይም አንካሳ፥ ወይም አፍንጫ ደፍጣጣ፥ ወይም፤ ትርፍ አካል ያለው፥ |
19. | ወይም እግረ ሰባራ፥ ወይም እጀ ሰባራ፥ |
20. | ወይም ጐባጣ፥ ወይም ድንክ፥ ወይም ዓይነ መጭማጫ፥ ወይም እከካም፥ ወይም ቋቍቻም፥ ወይም ጃንደረባ፥ ነውረኛ ሁሉ አይቅረብ። |
21. | ከካህኑ ከአሮን ዘር ነውር ያለበት ሰው የእግዚአብሔርን የእሳት ቍርባን ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ፤ ነውረኛ ነው፤ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ። |
22. | የቅዱሱንና የቅዱስ ቅዱሳኑን የአምላኩን እንጀራ ይብላ፤ |
23. | ነገር ግን ነውረኛ ነውና መቅደሶቼን እንዳያረክስ ወደ መጋረጃው አይግባ፥ ወደ መሠዊያውም አይቅረብ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ። |
24. | ሙሴም ይህን ለአሮን፥ ለልጆቹም፥ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ ነገረ። |
← Leviticus (21/27) → |