← Leviticus (2/27) → |
1. | ማናቸውም ሰው የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ሲያቀርብ ቍርባኑ ከመልካም ዱቄት ይሁን፤ ዘይትም ያፈስስበታል፥ ዕጣንም ይጨምርበታል፤ |
2. | ወደ አሮንም ልጆች ወደ ካህናቱ ያመጣዋል፤ ከመልካም ዱቄቱና ከዘይቱም አንድ እፍኝ ሙሉና ዕጣኑን ሁሉ ወስዶ ካህኑ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። |
3. | ከእህሉም ቍርባን የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ለእግዚአብሔር የሚሆን የእሳት ቍርባን ቅዱስ ቅዱሳን ነው። |
4. | በእቶን የተጋገረውን የእህል ቍርባን ስታቀርብ በዘይት የተለወሰ የመልካም ዱቄት የቂጣ እንጐቻ ወይም በዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ይሁን። |
5. | ቍርባንህም በምጣድ የተጋገረ የእህል ቍርባን ቢሆን፥ በዘይት የተለወሰ የመልካም ዱቄት ቂጣ ይሁን። |
6. | ቈርሰህም ዘይት ታፈስስበታለህ፤ የእህል ቍርባን ነው። |
7. | ቍርባንህም በመቀቀያ የበሰለ የእህል ቍርባን ቢሆን፥ ዘይት የገባበት ከመልካም ዱቄት የተደረገ ይሁን። |
8. | ከዚህም የተደረገውን የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር ታመጣለህ፤ ለካህኑም ይሰጣል፥ እርሱም ወደ መሠዊያው ያቀርበዋል። |
9. | ካህኑም ከእህሉ ቍርባን መታሰቢያውን አንሥቶ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። |
10. | ከእህሉም ቍርባን የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ለእግዚአብሔር የሚሆን የእሳት ቍርባን ቅዱስ ቅዱሳን ነው። |
11. | እርሾ ያለበት ነገር ማርም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ይሆን ዘንድ አታቀርቡምና ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት የእህል ቍርባን ሁሉ እርሾ አይሁንበት። |
12. | እነዚህንም የበኵራት ቍርባን አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር ታቀርባላችሁ፤ እንደ ጣፋጭ ሽታ ግን በመሠዊያው ላይ አይቃጠሉም። |
13. | የምታቀርበውን የእህል ቍርባን ሁሉ በጨው ታጣፍጠዋለህ፤ የአምላክህንም ቃል ኪዳን ጨው ከእህል ቍርባንህ አታጐድልም፤ በቍርባንህ ሁሉ ላይ ጨው ታቀርባለህ። |
14. | ከበኵራትም የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ብታቀርብ ስለዚህ ቍርባን በእሳት የተጠበሰና የተፈተገ የእህል እሸት ታቀርባለህ። |
15. | ዘይትም ታፈስስበታለህ፥ ዕጣንም ትጨምርበታለህ፤ የእህል ቍርባን ነው። |
16. | ካህኑም ከተፈተገው እህል ከዘይቱም ወስዶ ከዕጣኑ ሁሉ ጋር መታሰቢያውን ያቃጥላል፤ ይህ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነው። |
← Leviticus (2/27) → |