Leviticus (19/27)  

1. እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2. ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ ባላቸው። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ።
3. ከእናንተ ሰው ሁሉ እናቱንና አባቱን ይፍራ፥ ሰንበታቴንም ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
4. ወደ ጣዖታትም ዘወር አትበሉ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም የአማልክት ምስሎች ለእናንተ አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
5. የደኅንነትንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ስትሰዉ እርሱን ደስ እንድታሰኙበት ሠዉት።
6. በምትሠዉት ቀንና በነጋው ይበላል፤ እስከ ሦስተኛውም ቀን ድረስ ቢተርፍ በእሳት ይቃጠላል።
7. በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ጸያፍ ነው፥ ደስም አያሰኝም፤
8. የበላውም ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን ነገር አርክሶአልና ኃጢአቱን ይሸከማል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።
9. የምድራችሁንም መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር ፈጽማችሁ አትጨዱ፥ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ።
10. የወይንህንም ቃርሚያ አትቃርም፥ የወደቀውንም የወይንህን ፍሬ አትሰብስብ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተወው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
11. አትስረቁ፥ አትካዱም፥ ከእናንተም እርስ በርሳችሁ ሐሰት አትነጋገሩ።
12. በስሜም በሐሰት አትማሉ፥ የአምላካችሁንም ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
13. በባልንጀራህ ግፍ አታድርግ፥ አትቀማውም። የሞያተኛው ዋጋ እስከ ነገ ድረስ በአንተ ዘንድ አይደርብህ።
14. ደንቆሮውን አትስደብ፥ በዕውርም ፊት ዕንቅፋት አታድርግ፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
15. በፍርድ ዓመፃ አታድርጉ፤ ለድሀ አታድላ፥ ባለ ጠጋውንም አታክብር፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በእውነት ፍረድ።
16. በሕዝብህ መካከል በሸንጋይነት አትዙር፤ በባልንጀራህም ደም ላይ አትቁም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
17. ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ በባልንጀራህ ምክንያት ኃጢአት እንዳይሆንብህ ገሥጸው።
18. አትበቀልም፥ በሕዝብህም ልጆች ቂም አትያዝ፥ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
19. ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህ ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፤ ከሁለት ዓይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ።
20. ማናቸውም ሰው ከሴት ባሪያ ጋር ቢተኛ፥ እርስዋም ለባል የተሰጠች ዋጋዋም ያልተከፈለ አርነት ያልወጣች ብትሆን፥ ቅጣት አለባቸው፤ አርነት አልወጣችምና አይገደሉም።
21. እርሱም የበደሉን መሥዋዕት ይዞ ወደ እግዚአብሔር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይመጣል፥ ለበደልም መሥዋዕት አውራ በግ ያመጣል።
22. ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት በበደል መሥዋዕት በግ ያስተሰርይለታል፤ የሠራውም ኃጢአት ይቀርለታል።
23. ወደ አገሩም በገባችሁ ጊዜ፥ የሚበላ የፍሬ ዛፍ ሁሉ በተከላችሁም ጊዜ፥ ፍሬውን እንዳልተገረዘ ትቈጥሩታላችሁ፤ ሦስት ዓመት እንዳልተገረዘ ይሆንላችኋል፤ አይበላም።
24. የአራተኛውም ዓመት ፍሬ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና ቅዱስ ይሁን።
25. ፍሬውም ይበዛላችሁ ዘንድ የአምስተኛውን ዓመት ፍሬ ብሉ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
26. ከደሙ ጋር ምንም አትብሉ፤ አስማትም አታድርጉ፥ ሞራ ገላጭም አትሁኑ።
27. የራስ ጠጕራችሁንም ዙሪያውን አትከርክሙት፥ ጢማችሁንም ዙሪያውን አትቍረጡት።
28. ስለ ሞተውም ሥጋችሁን አትንጩ፥ ገላችሁንም አትንቀሱት፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
29. ምድሪቱ ከግልሙትና ከርኵሰትም እንዳትሞላ ሴት ልጅህን ታመነዝር ዘንድ አታርክሳት።
30. ሰንበታቴን ጠብቁ፥ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
31. ወደ መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች አትሂዱ፤ እንዳትረክሱባቸውም አትፈልጉአቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
32. በሽበታሙ ፊት ተነሣ፥ ሽማግሌውንም አክብር፥ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
33. በአገራችሁ ውስጥ ከእናንተ ጋር እንግዳ ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት።
34. እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ፥ እርሱንም እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
35. በፍርድ፥ በመለካትም፥ በመመዘንም፥ በመስፈርም ዓመፃ አታድርጉ።
36. የእውነትም ሚዛን፥ የእውነትም መመዘኛ፥ የእውነትም የኢፍ መስፈሪያ፥ የእውነትም የኢን መስፈሪያ ይሁንላችሁ፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እኔ ነኝ።
37. ሥርዓቴን ሁሉ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ አድርጉም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

  Leviticus (19/27)