| ← Leviticus (18/27) → |
| 1. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 2. | ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። |
| 3. | እንደ ተቀመጣችሁባት እንደ ግብፅ ምድር ሥራ አትሥሩ፤ እኔም ወደ እርስዋ እንደማገባችሁ እንደ ከነዓን ምድር ሥራ አትሥሩ፤ በሥርዓታቸውም አትሂዱ። |
| 4. | ፍርዴን አድርጉ፥ በእርስዋም ትሄዱ ዘንድ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። |
| 5. | የሚሠራቸው ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራልና ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። |
| 6. | ከእናንተም ማንም ሰው ኃፍረተ ሥጋውን ይገልጥ ዘንድ ወደ ዘመዱ ሁሉ አይቅረብ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። |
| 7. | የአባትህን ኃፍረተ ሥጋና የእናትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ እናትህ ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። |
| 8. | የአባትህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህን ኃፍረተ ሥጋ ነው። |
| 9. | የእኅትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ልጅ ወይም የእናትህ ልጅ፥ በቤት ወይም በውጭ የተወለደች ብትሆን፥ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። |
| 10. | የወንድ ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ወይም የሴት ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአንተ ኃፍረተ ሥጋ ነውና። |
| 11. | ከአባትህ የተወለደችውን የአባትህን ሚስት ልጅ ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ እህትህ ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። |
| 12. | የአባትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ዘመድ ናት። |
| 13. | የእናትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የእናትህ ዘመድ ናት። |
| 14. | የአባትህን ወንድም ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፥ ወደ ሚስቱም አትቅረብ፤ የአጎትህ ሚስት ናት። |
| 15. | የምራትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የልጅህ ሚስት ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። |
| 16. | የወንድምህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድምህ ኃፍረተ ሥጋ ነው። |
| 17. | የሴትንና የሴት ልጅዋን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድ ልጅዋን ሴት ልጅ ወይም የሴት ልጅዋን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ትግለጥ ዘንድ አታግባ፤ ዘመዶች ናቸው፤ ዝሙት ነው። |
| 18. | ሚስትህ በሕይወት ሳለች እኅትዋ ጣውንትዋ እንዳትሆን፥ ኃፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ ከእርስዋ ጋር እኅትዋን አታግባ። |
| 19. | እርስዋም በመርገምዋ ርኵሰት ሳለች ኃፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ ወደ ሴት አትቅረብ። |
| 20. | እንዳትረክስባትም ከባልንጀራህ ሚስት ጋር አትተኛ። |
| 21. | ከዘርህም ለሞሎክ በእሳት አሳልፈህ አትስጥ፥ የአምላክህንም ስም አታርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። |
| 22. | ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ጸያፍ ነገር ነውና። |
| 23. | እንዳትረክስባትም ከእንሰሳ ጋር አትተኛ፤ ሴት ከእርሱ ጋር ትተኛ ዘንድ በእንስሳ ፊት አትቁም፤ የተጠላ ነገር ነውና። |
| 24. | በእነዚህ ሁሉ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አትርከሱ። |
| 25. | ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ኃጢአትዋን በእርስዋ ላይ እመልሳለሁ፥ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች ትተፋለች። |
| 26. | ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እናንተም የአገሩ ልጆች በእናንተም መካከል የሚኖሩት እንግዶች ከዚህ ርኵሰት ምንም አትሥሩ፤ |
| 27. | ከእናንተ በፊት የነበሩ የአገሩ ልጆች ይህን ርኵሰት ሁሉ ሠርተዋልና፥ ምድሪቱም ረክሳለችና፤ |
| 28. | ባረከሳችኋት ጊዜ ምድሪቱ ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ እንደ ተፋች እናንተን እንዳትተፋችሁ። |
| 29. | ከዚህ ርኵሰት ሁሉ ማናቸውን የሚያደርግ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋልና። |
| 30. | ስለዚህ ከእናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች የሠሩትን ጸያፍ የሆነውን ወግ ሁሉ እንዳትሠሩ፥ በእርሱም እንዳትረክሱ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። |
| ← Leviticus (18/27) → |