← Leviticus (17/27) → |
1. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
2. | ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገር። እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፥ እንዲህም አለ። |
3. | ከእስራኤል ቤት ማናቸውም ሰው በሬ ወይም በግ ወይም ፍየል ቢያርድ፥ በሰፈሩ ውስጥ ወይም ከሰፈሩ ውጭ ቢያርደው፥ |
4. | በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ለእግዚአብሔር ቍርባን ያቀርብ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ደሙ በዚያ ሰው ላይ ይቈጠርበታል፤ ደም አፍስሶአል፤ ያም ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። |
5. | ስለዚህ የእስራኤል ልጆች በሜዳ የሚያርዱትን መሥዋዕታቸውን ወደ እግዚአብሔር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ያመጡታል፤ ወደ ካህኑም አምጥተው ለእግዚአብሔር ለደኅንነት መሥዋዕት ይሠዉታል። |
6. | ካህኑም በመገኛኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ደሙን ይረጨዋል፥ ስቡንም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ያቃጥለዋል። |
7. | መሥዋዕታቸውንም ደግሞ ተከትለው ላመነዘሩባቸው ለሰይጣናት አይሠዉ። ይህ ለእነርሱ ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ሥርዓት ይሁን። |
8. | ለእነርሱም እንዲህ በላቸው። ከእስራኤል ቤት በመካከላቸውም ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥ |
9. | ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። |
10. | ከእስራኤልም ልጆች ወይም በመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው ደም ቢበላ፥ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ፥ ያንንም ሰው ከሕዝቡ ለይቼ አጠፋዋለሁ። |
11. | የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት። |
12. | ስለዚህ የእስራኤልን ልጆች። ከእናንተ ማንም ደምን አይበላም፥ በመካከላችሁም ከሚኖሩ እንግዶች ማንም ደምን አይበላም አልሁ። |
13. | ከእስራኤልም ልጆች በመካከላቸውም ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚበላ እንስሳ ወይም ወፍ እያደነ ቢይዝ፥ ደሙን ያፈስሳል በአፈርም ይከድነዋል። |
14. | የሥጋ ሁሉ ሕይወትና ደሙ አንድ ነውና ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች። የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የሥጋውን ሁሉ ደም አትብሉ፤ የሚበላውም ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ አልኋቸው። |
15. | የሞተውን ወይም አውሬ የሰበረውን የሚበላ ሰው ሁሉ፥ የአገር ልጅ ወይም እንግዳ ቢሆን፥ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። |
16. | ልብሱንና ገላውን ባያጥብ ግን ኃጢአቱን ይሸከማል። |
← Leviticus (17/27) → |