Leviticus (15/27)  

1. እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
2. ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብላችሁ ንገሩአቸው። ማንም ሰው ከሥጋው ፈሳሽ ነገር ቢወጣ፥ ስለሚፈስሰው ነገር ርኩስ ነው።
3. ስለሚፈስሰው ነገር ርኵስነቱ ይህ ነው፤ ፈሳሹ ነገር ከሥጋው ቢፈስስ ወይም ከመፍሰሱ ቢቆም፥ ርኩስ መሆኑ ነው።
4. ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚተኛበት መኝታ ሁሉ ርኩስ ነው፤ የሚቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው።
5. መኝታውንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
6. ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በተቀመጠበት ነገር ላይ የሚቀመጥበት ሰው ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
7. ፈሳሽ ነገር ያለበትን የሰውን ሥጋ የሚነካ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
8. ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በንጹሕ ሰው ላይ ቢተፋ፥ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
9. ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የተቀመጠበት ኮርቻ ሁሉ ርኩስ ነው።
10. ከበታቹም ያለውን ነገር የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው፤ እነዚህንም ነገሮች የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
11. ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው እጁን በውኃ ሳይታጠብ የሚነካው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
12. ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚነካውን የሸክላ ዕቃ ይስበሩት፤ የእንጨቱም ዕቃ ሁሉ በውኃ ይታጠብ።
13. ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው ከፈሳሹ ነገር ሲነጻ ስለ መንጻቱ ሰባት ቀን ይቈጥራል፤ ልብሱንም ያጥባል፥ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል።
14. በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዞ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ይመጣል፥ ለካህኑም ይሰጣቸዋል።
15. ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ፈሳሹ ነገር ያስተሰርይለታል።
16. የማንም ሰው ዘር ከእርሱ ቢወጣ፥ ገላውን ሁሉ በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
17. ዘር የነካው ልብስ ሁሉ ቁርበትም ሁሉ በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
18. ወንዱ በሴቲቱ ቢደርስባት ሁለቱ በውኃ ይታጠባሉ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩሶች ናቸው።
19. ሴት ፈሳሽ ነገር ቢኖርባት በሥጋዋም ያለው ፈሳሽ ነገር ደም ቢሆን፥ በመርገምዋ ሰባት ቀን ትቀመጣለች፤ የሚነካትም ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው።
20. መርገምም ስትሆን የምትተኛበት ነገር ሁሉ ርኩስ ነው፤ የምትቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው።
21. መኝታዋንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
22. የምትቀመጥበትንም ነገር ሁሉ የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
23. በመኝታዋም ላይ ወይም በምትቀመጥበት ነገር ላይ ቢሆን ሲነካው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው።
24. ማንም ከእርስዋ ጋር ቢተኛ መርገምዋም ቢነካው፥ ሰባት ቀን ርኩስ ነው፤ የሚተኛበትም መኝታ ሁሉ ርኩስ ነው።
25. ሴትም ከመርገም ቀን ሌላ ደምዋ ብዙ ቀን ቢፈስስ፥ ወይም ደምዋ ከመርገምዋ ወራት የሚበልጥ ቢፈስስ፥ በመርገምዋ ወራት እንደ ሆነች እንዲሁ በፈሳሽዋ ርኵስነት ወራት ትሆናለች፤ ርኩስ ናት።
26. ደምዋም በሚፈስስበት ወራት ሁሉ የምትተኛበት መኝታ ሁሉ በመርገምዋ ጊዜ እንደ ነበረው መኝታ ያለ ይሆንባታል፤ የምትቀመጥበት ነገር ሁሉ እንደ መርገምዋ ርኵስነት ርኵስ ነው።
27. እነዚህንም ነገሮች የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው፤ ልብሱንም ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
28. ከፈሳሽዋም ብትነጻ ሰባት ቀን ትቈጥራለች ከዚያም በኋላ ንጹሕ ትሆናለች።
29. በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዛ ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ታመጣቸዋለች።
30. ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም ስለ ፈሳሽዋ ርኵስነት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል።
31. እንዲሁም በእነርሱ መካከል ያለችውን ማደሪያዬን ባረከሱ ጊዜ፥ በርኵስነታቸው እንዳይሞቱ የእስራኤልን ልጆች ከርኵስነታቸው ለያቸው።
32. ፈሳሽ ነገር ላለበት ሰው፥ ይረክስም ዘንድ ዘሩ ለሚወጣበት ሰው፥
33. በመርገምዋም ለታመመች፥ ፈሳሽም ነገር ላለባቸው ለወንድም ለሴትም፥ የረከሰችንም ሴት ለሚገናኝ ሰው ሕጉ ይኸው ነው።

  Leviticus (15/27)