Leviticus (14/27)  

1. እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።
2. በመንጻቱ ቀን የለምጻሙ ሕግ ይህ ይሆናል፤ ወደ ካህኑ ይወስዱታል።
3. ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ከለምጻሙ ላይ ቢጠፋ፥
4. ካህኑ ስለሚነጻው ሰው ሁለት ንጹሐን ወፎች በሕይወታቸው፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ያመጣ ዘንድ ያዝዛል።
5. ካህኑም ከሁለቱ ወፎች አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርድ ዘንድ ይዝዛል።
6. ሕያውንም ወፍ ዝግባውንም እንጨት ቀዩንም ግምጃ ሂሶጱንም ወስዶ ከሕያው ወፍ ጋር በምንጭ ውኃ ላይ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይነክራቸዋል።
7. ከለምጹ በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጫል፤ ንጹሕም ነው ይለዋል፥ ሕያውንም ወፍ ወደ ሜዳ ይለቅቀዋል።
8. የነጻውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ጠጕሩንም ሁሉ ይላጫል፥ በውኃም ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል። ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል፥ ነገር ግን ከድንኳኑ በውጭ ሆኖ ሰባት ቀን ይቀመጣል።
9. በሰባተኛውም ቀን ጠጕሩን ሁሉ ይላጫል፤ ራሱንም፥ ጢሙንም፥ ቅንድቡንም፥ የገላውንም ጠጕር ሁሉ ይላጫል፤ ልብሱንም፥ ገላውንም በውኃ ያጥባል፤ ንጹሕም ይሆናል።
10. በስምንተኛውም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባት ጠቦት፥ ነውር የሌለባትንም አንዲት የዓመት እንስት ጠቦት፥ ስለ እህልም ቍርባን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ አንድ የሎግ መስፈሪያም ዘይት ይወስዳል።
11. የሚያነጻውም ካህን እነዚህን ነገሮች የሚነጻውንም ሰው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ያኖራቸዋል።
12. ካህኑም አንዱን ጠቦት ወስዶ ስለ በደል መሥዋዕት ያቀርበዋል፥ ያንንም የሎግ መስፈሪያ ዘይት፤ ስለ መወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዘዋል።
13. የኃጢአትን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት በተቀደሰው ስፍራ ጠቦቱን ያርደዋል፤ የኃጢአቱ መሥዋዕት ለካህኑ እንደሚሆን፥ እንዲሁ የበደል መሥዋዕት ነው፤ ቅዱስ ቅዱሳን ነው።
14. ካህኑም ከበደል መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል።
15. ካህኑም ከዘይቱ ከሎግ መስፈሪያው ወስዶ በግራ እጁ ውስጥ ያፈስሰዋል።
16. ካህኑም በግራ እጁ ውስጥ ባለው ዘይት ቀኝ ጣቱን ነክሮ ከዘይቱ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል።
17. ካህኑም በእጁ ውስጥ ከቀረው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት የበደል መሥዋዕት ደም ባረፈበት ላይ ያስነካዋል።
18. በካህኑም እጅ ውስጥ የቀረውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርግበታል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል።
19. ካህኑም የኃጢአቱን መሥዋዕት ያቀርባል፥ ከርኵሰቱም ለሚነጻው ሰው ያስተሰርይለታል፤ በኋላም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያርዳል።
20. ካህኑም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን በመሠዊያው ላይ ያቀርባል፥ ካህኑም ያስተሰርይለታል፤ እርሱም ንጹሕ ይሆናል።
21. ድሀም ቢሆን ይህንም ለማምጣት ገንዘቡ ባይበቃው፥ ማስተስረያ ይሆንለት ዘንድ እንዲወዘወዝ አንድ ጠቦት ለበደል መሥዋዕት፥ ከመስፈሪያውም ከአሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን፥ አንድ የሎግ መስፈሪያም ዘይት ይወስዳል።
22. ሁለት ዋኖሶች ወይም የርግብ ግልገሎች እንደሚቻለው፥ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ይወስዳል።
23. በስምንተኛውም ቀን ስለ መንጻት ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣቸዋል።
24. ካህኑም የበደሉን መሥዋዕት ጠቦት የሎግ መስፈሪያውንም ዘይት ይወስዳል፤ ካህኑም ለመወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል።
25. የበደሉንም መሥዋዕት ጠቦት ያርዳል፤ ካህኑም ከበደሉ መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል።
26. ካህኑም ከዘይቱ በግራ እጁ ውስጥ ያፈስሰዋል።
27. ካህኑም በግራ እጁ ውስጥ ካለው ዘይት በቀኝ ጣቱ ሰባት ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ይረጨዋል።
28. ካህኑም በእጁ ውስጥ ካለው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት የበደል መሥዋዕት ደም ባረፈበት ላይ ያስነካዋል።
29. በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለት ዘንድ በካህኑ እጅ ውስጥ የቀረውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርገዋል።
30. እንደሚቻለው ከዋኖሶች ወይም ከርግብ ግልገሎች አንዱን ያቀርባል።
31. እንደሚቻለው አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ከእህል ቍርባን ጋር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል ካህኑም ለሚነጻው ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል።
32. ለመንጻቱ የሚያስፈልገውን ነገር ለማያገኝ የለምጽ ደዌ ላለበት ሰው ሕግ ይህ ነው።
33. እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
34. ወደምሰጣችሁ ርስት ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ እኔም የለምጽ ደዌ በርስታችሁ ምድር በአንድ ቤት ባደረግሁ ጊዜ፥
35. ባለቤቱ መጥቶ ካህኑን። ደዌ በቤቴ ውስጥ እንዳለ ይመስለኛል ብሎ ይንገረው።
36. ካህኑም በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዳይረክስ፥ እርሱ ደዌውን ለማየት ወደ ቤት ሳይገባ፥ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ያዝዛል፤ በኋላም ካህኑ ቤቱን ለማየት ይገባል።
37. ደዌውንም ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በግንቡ ላይ በአረንጓዴና በቀይ ቢዥጐረጐር፥ መልኩም ወደ ግንቡ ውስጥ ቢጠልቅ፥
38. ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ቤቱ በር ወጥቶ ሰባት ቀን ቤቱን ይዘጋዋል።
39. ካህኑም በሰባተኛው ቀን ተመልሶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግንብ ላይ ቢሰፋ፥
40. ካህኑ ደዌ ያለባቸውን ድንጋዮች እንዲያወጡ፥ ከከተማውም ወደ ውጭ ወደ ረከሰው ስፍራ እንዲጥሉአቸው ያዝዛል።
41. ቤቱንም በውስጡ በዙሪያው ያስፍቀዋል፤ የፋቁትንም የምርጊቱን አፈር ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ረከሰ ስፍራ ያፈስሱታል።
42. በእነዚያም ድንጋዮች ስፍራ ሌሎች ድንጋዮች ያገባሉ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይመርጉታል።
43. ደዌውም ዳግም ቢመለስ፥ ድንጋዮቹም ከወጡ ቤቱም ከተፋቀና ከተመረገ በኋላ በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥
44. ካህኑ ገብቶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ በቤቱ ውስጥ ያለው እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው።
45. ቤቱንም፥ ድንጋዮቹንም፥ እንጨቱንም፥ የቤቱንም ምርጊት ሁሉ ያፈርሳል፤ እነርሱንም ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ርኩስ ስፍራ ያወጣል።
46. በተዘጋበትም ጊዜ ሁሉ ወደ ቤቱ የሚገባ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
47. በቤቱም የሚተኛ ልብሱን ያጥባል፤ በቤቱም የሚበላ ልብሱን ያጥባል።
48. ካህኑም ገብቶ ቢያይ፥ እነሆም፥ ቤቱ ከተመረገ በኋላ ደዌው በቤቱ ውስጥ ባይሰፋ፥ ደዌው ስለ ሻረ ካህኑ ቤቱን። ንጹሕ ነው ይለዋል።
49. ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ይወስዳል።
50. አንደኛውንም ወፍ በሸክላ ዕቃ ውስጥ ከምንጩ ውኃ በላይ ያርዳል።
51. የዝግባውን እንጨት፥ ሂሶጱንም፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ሕያውንም ወፍ ወስዶ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውኃ ውስጥ ይነክራቸዋል፥ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይረጨዋል።
52. ቤቱንም በወፉ ደም በምንጩም ውኃ በሕያውም ወፍ በዝግባውም እንጨት በሂሶጱም በቀዩም ግምጃ ያነጻዋል።
53. ሕያውንም ወፍ ከከተማ ወደ ሜዳ ይሰድደዋል፤ ለቤቱም ያስተሰርይለታል፥ ንጹሕም ይሆናል።
54. ይህም ሕግ ነው ለሁሉ ዓይነት ለምጽ ደዌ፥
55. ለቈረቈርም፥ በልብስና በቤትም ላለ ለምጽ፥
56. ለእባጭም፥ ለብጕርም፥ ለቋቁቻም፤
57. በሚረክስና በሚነጻ ጊዜ እንዲያስታውቅ ይህ የለምጽ ሕግ ነው።

  Leviticus (14/27)