Leviticus (13/27)  

1. እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
2. ማናቸውም ሰው በሥጋው ቁርበት ላይ እባጭ ወይም ብጕር ወይም ቋቁቻ ቢታይ፥ በሥጋው ቁርበት እንደ ለምጽ ደዌ ቢመስል፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ከካህናቱ ልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት።
3. ካህኑም በሥጋው ቁርበት ያለውን ደዌ ያያል፤ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ ደዌውም ወደ ሥጋው ቁርበት ቢጠልቅ፥ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው፤ ካህኑም አይቶ። ርኩስ ነው ይበለው።
4. ቋቁቻውም በሥጋው ቁርበት ላይ ቢነጣ፥ ከቁርበቱም የጠለቀ ባይመስል፥ ጠጕሩም ባይነጣ፥ ካህኑ የታመመውን ሰው ሰባት ቀን ይዘጋበታል።
5. በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው በዓይኑ ፊት እንደ ነበረ ቢሆን፥ በቁርበቱም ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ ሰባት ቀን ደግሞ ይዘጋበታል።
6. ደግሞ በሰባተኛው ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢከስም፥ ደዌውም በቁርበቱ ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ እከክ ነው፤ ልብሱንም አጥቦ ንጹሕ ይሆናል።
7. ስለ መንጻቱ በካህኑ ዘንድ ከታየ በኋላ እከኩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ እንደ ገና ሊታይ ወደ ካህኑ ይቀርባል።
8. ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ እከኩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ ለምጽ ነው።
9. የለምጽ ደዌ በሰው ውስጥ ቢሆን እርሱን ወደ ካህኑ ያመጡለታል።
10. ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ በቁርበቱ ላይ ነጭ እባጭ ቢሆን፥ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥
11. እርሱ በሥጋው ቁርበት ላይ አሮጌ ለምጽ ነው፥ ካህኑም። ርኩስ ነው ይለዋል፤ እርሱ ርኩስ ነውና አይዘጋበትም።
12. ለምጹም በቁርበቱ ላይ ሰፍቶ ቢወጣ፥ ለምጹም የታመመውን ሰው ቁርበቱን ሁሉ ከራሱ እስከ እግሮቹ ድረስ እንደ ከደነው ለካህኑ ቢመስለው፥ ካህኑ ያያል፤
13. እነሆም፥ ለምጹ ሥጋውን ሁሉ ቢከድን የታመመውን ሰው። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ሥጋው ሁሉ ፈጽሞ ተለውጦ ነጭ ሆኖአል፤ ንጹሕ ነው።
14. የሚያዠው ሥጋ ግን ሲታይበት ርኩስ ይሆናል።
15. ካህኑም የሚያዠውን ሥጋ አይቶ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የሚያዠው ሥጋ ለምጽ ነውና ርኩስ ነው።
16. የሚያዠውም ሥጋ ተለውጦ ቢነጣ እንደ ገና ወደ ካህኑ ይመጣል።
17. ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢነጣ ካህኑ የታመመውን። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ንጹሕ ነው።
18. በሥጋውም ቁርበት ላይ ቍስል ቢሆንና ቢሽር፥
19. በቍስሉም ስፍራ ነጭ እባጭ ወይም ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢወጣ፥ በካህኑ ዘንድ ይታያል።
20. ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ ወደ ቁርበቱ ውስጥ ጠልቆ ቢታይ፥ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከቍስሉ ውስጥ ወጥቶአል።
21. ካህኑም ቢያየው፥ ነጭም ጠጕር ባይኖርበት፥ ወደ ቁርበቱም ውስጥ ባይጠልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይዘጋበታል።
22. በቁርበቱም ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌ ነው።
23. ቋቁቻው ግን በስፍራው ቢቆም ባይሰፋም፥ የቍስል ጠባሳ ነው፤ ካህኑም። ንጹሕ ነው ይለዋል።
24. በሥጋውም ቁርበት የእሳት ትኵሳት ቢኖርበት፥ በተቃጠለውም ስፍራ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢታይ፥
25. ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ በቋቁቻው ጠጕሩ ተለውጦ ቢነጣ፥ ወደ ቁርበቱም ውስጥ ቢጠልቅ፥ ለምጽ ነው፤ ከተቃጠለውም ስፍራ ወጥቶአል፤ ካህኑም። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው።
26. ካህኑም ቢያየው፥ በቋቁቻውም ነጭ ጠጕር ባይኖር፥ ወደ ቁርበቱም ባይጠልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይዘጋበታል።
27. ካህኑም በሰባተኛው ቀን ያየዋል፤ በቁርበቱም ላይ ቢሰፋ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው።
28. ቋቁቻውም በስፍራው ላይ ቢቆም፥ በቁርበቱም ላይ ባይሰፋ ነገር ግን ቢከስም፥ የትኵሳት እባጭ ነው፤ የትኵሳትም ጠባሳ ነውና ካህኑ። ንጹሕ ነው ይለዋል።
29. ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በራሱ ወይም በአገጩ ደዌ ቢኖርበት፥
30. ካህኑ ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ወደ ቁርበቱ ቢጠልቅ፥ በውስጡም ቀጭን ብጫ ጠጕር ቢኖርበት፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ ቈረቈር ነው፤ የራስ ወይም የአገጭ ለምጽ ነው።
31. ካህኑም የቈረቈሩን ደዌ ቢያይ፥ ወደ ቁርበቱም ባይጠልቅ፥ ጥቁርም ጠጕር ባይኖርበት፥ ካህኑ የቈረቈር ደዌ ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይዘጋበታል።
32. ካህኑም በሰባተኛው ቀን ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ ባይሰፋ፥ በውስጡም ብጫ ጠጕር ባይኖር፥ የቈረቈሩም መልክ ወደ ቁርበቱ ባይጠልቅ፥ ይላጫል፥
33. ቈረቈሩ ግን አይላጭም፤ ካህኑም ቈረቈር ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ደግሞ ይዘጋበታል።
34. ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቈረቈሩን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ባይሰፋ፥ መልኩም ወደ ቁርበቱ ባይጠልቅ፥ ካህኑ። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ልብሱን አጥቦ ንጹሕ ይሆናል።
35. ከነጻ በኋላ ግን ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ ያየዋል፤
36. እነሆም፥ ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ ካህኑ ብጫውን ጠጕር አይፈልግም፤ ርኩስ ነው።
37. ቈረቈሩ ግን በዓይኑ ፊት እንደ ነበረ ቢሆን፥ ጥቁርም ጠጕር ቢበቅልበት፥ ቈረቈሩ ሽሮአል እርሱም ንጹሕ ነው፤ ካህኑም። ንጹሕ ነው ይለዋል።
38. ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በሥጋው ቁርበት ላይ ነጭ ቋቁቻ ቢኖርበት፥
39. ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ በሥጋቸው ቁርበት ላይ ያለው ቋቁቻ ፈገግ ቢል አጓጐት ነው፤ ከቁርበቱ ውስጥ ወጥቶአል፤ ንጹሕ ነው።
40. የሰውም ጠጕር ከራሱ ቢመለጥ እርሱ ቡሀ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው።
41. ጠጕሩም ከግምባሩ ቢመለጥ እርሱ ራሰ በራ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው።
42. በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ደዌ ቢኖርበት፥ እርሱ ከቡሀነቱ ወይም ከራሰ በራነቱ የወጣ ለምጽ ነው።
43. ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ የደዌው እብጠት፥ በሥጋው ቁርበት ላይ የሆነ ለምጽ መስሎ፥ በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ቢሆን፥
44. ለምጻም ሰው ነው፤ ርኩስ ነው፤ ካህኑ። በእርግጥ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌው በራሱ ነው።
45. የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው ልብሱ የተቀደደ ይሁን፥ ራሱም የተገለጠ ይሁን፥ ከንፈሩንም ይሸፍን፤ ርኩስ ርኩስ ነኝ ይበል።
46. ደዌው ባለበት ዘመን ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር በውጭ ይሆናል።
47. የለምጽም ደዌ በልብስ ላይ ቢሆን፥ ልብሱም የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ቢሆን፥
48. በድሩ ወይም በማጉ ላይ ቢሆን፥ በፍታ ወይም የበግ ጠጕር ቢሆን፥ አጐዛ ወይም ከአጐዛ የሚደረግ ነገር ቢሆን፥
49. ደዌው በልብሱ ወይም በአጐዛው ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛው በሚደረገው ነገር አረንጓዴ ወይም ቀይ ቢሆን፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ለካህኑ ይታያል።
50. ካህኑም ደዌውን አይቶ ደዌው ያለበትን ነገር ሰባት ቀን ይዘጋበታል።
51. በሰባተኛውም ቀን ደዌውን ያያል፤ ደዌውም በልብስ ላይ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በአጐዛው ወይም ከአጐዛው በሚደረግ ነገር ቢሰፋ፥ ደዌው እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው።
52. ልብሱን ያቃጥል፤ ድሩ ወይም ማጉ የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ቢሆን ወይም ከአጐዛው የተደረገ ቢሆን፥ ደዌ ያለበት ሁሉ፥ እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነውና በእሳት ይቃጠል።
53. ካህኑ ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛ በተደረገ ነገር ቢሆን በልብሱ ላይ ባይሰፋ፥
54. ካህኑ ደዌ ያለበቱ ነገር እንዲታጠብ ይዘዝ፤ ሌላም ሰባት ቀን ይዘጋበታል።
55. ደዌውም ከታጠበ በኋላ ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው መልኩን ባይለውጥ ባይሰፋም፥ ርኩስ ነው፤ በእሳት አቃጥለው፤ ምልክቱ በውስጥ ወይም በውጭ ቢሆን እየፋገ የሚሄድ ደዌ ነው።
56. ካህኑም ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው ከታጠበ በኋላ ቢከስም፥ ከልብሱ ወይም ከአጐዛው ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ይቅደደው።
57. በልብሱም ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛው በተደረገ ነገር ላይ ደግሞ ቢታይ፥ የወጣ ለምጽ ነው፤ ደዌው ያለበትን ነገር አቃጥለው።
58. አንተም ካጠብኸው ልብስ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ወይም ከአጐዛው ከተደረገው ነገር ላይ ደዌው ቢጠፋ፥ ሁለተኛ ጊዜ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል።
59. በበግ ጠጕር ልብስ ወይም በበፍታ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛ በተደረገ ነገር ላይ ቢሆን፥ ንጹሕ ወይም ርኩስ ያሰኝ ዘንድ የለምጽ ደዌ ሕግ ይህ ነው።

  Leviticus (13/27)