| ← Lamentations (2/5) → |
| 1. | አሌፍ። ጌታ በቍጣው የጽዮንን ሴት ልጅ እንደ ምን አደመናት! የእስራኤልን ውበት ከሰማይ ወደ ምድር ጣለ፥ በቍጣውም ቀን የእግሩን መረገጫ አላሰበም። |
| 2. | ቤት። ጌታ የያዕቆብን ማደሪያዎች ሁሉ ዋጠ፥ አልራራምም፤ በመዓቱ የይሁዳን ሴት ልጅ አምቦች አፈረሰ፥ ወደ ምድርም አወረዳቸው፤ መንግሥቱንና አለቆችዋን አረከሰ። |
| 3. | ጋሜል። በጽኑ ቍጣው የእስራኤልን ቀንድ ሁሉ ቀጠቀጠ፤ ቀኝ እጁን ከጠላት ፊት ወደ ኋላ መለሰ፥ በዙሪያውም እንደሚባላ እንደ እሳት ነበልባል ያዕቆብን አቃጠለ። |
| 4. | ዳሌጥ። ቀስቱን እንደ ጠላት ገተረ፥ እንደ አስጨናቂ ቀኝ እጁን አጸና፥ ለዓይንም የሚያምረውን ሁሉ ገደለ፤ በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳን መዓቱን እንደ እሳት አፈሰሰ። |
| 5. | ሄ። ጌታ እንደ ጠላት ሆነ፥ እስራኤልን ዋጠ፤ አዳራሾችዋን ሁሉ ዋጠ፥ አምቦችዋን አጠፋ፤ በይሁዳም ሴት ልጅ ኀዘንና ልቅሶ አበዛ። |
| 6. | ዋው። ማደሪያውን እንደ አትክልት ነቀለ፤ የበዓሉን ስፍራ አጠፋ፤ እግዚአብሔር በጽዮን ዓመት በዓሉንና ሰንበቱን አስረሳ፥ በቍጣውም መዓት ንጉሡንና ካህኑን አቃለለ። |
| 7. | ዛይ። ጌታ መሠዊያውን ጣለ፥ መቅደሱን ጠላ፥ የአዳራሾችዋንም ቅጥር በጠላት እጅ አሳልፎ ሰጠ፤ ድምፃቸውን እንደ ዓመት በዓል ቀን በእግዚአብሔር ቤት ከፍ ከፍ አደረጉ። |
| 8. | ሔት። እግዚአብሔር የጽዮንን ሴት ልጅ ቅጥር ያፈርስ ዘንድ አሰበ፤ የመለኪያውን ገመድ ዘረጋ፥ እጁን ከማጥፋት አልመለሰም፤ ምሽጉና ቅጥሩ እንዲያለቅሱ አደረገ፤ በአንድነት ደከሙ። |
| 9. | ጤት። በሮችዋ በመሬት ውስጥ ሰጠሙ፥ መወርወሪያዎችዋን አጠፋ ሰበረም፤ ንጉሥዋና አለቆችዋ ሕግ በሌለባቸው በአሕዛብ መካከል አሉ፤ ነቢያቶቻዋም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አላገኙም። |
| 10. | ዮድ። የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች ዝም ብለው በመሬት ላይ ተቀምጠዋል፤ ትቢያን በራሳቸው ላይ ነሰነሱ፥ ማቅም ታጠቁ፤ የኢየሩሳሌም ደናግል ራሳቸውን ወደ ምድር አዘነበሉ። |
| 11. | ካፍ። ሕፃኑና ጡት የሚጠባው በከተማይቱ ጐዳና ላይ ሲዝሉ፥ ዓይኔ በእንባ ደከመች፥ አንጀቴም ታወከ፤ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ። |
| 12. | ላሜድ። በከተማ ጐዳና እንደ ተወጋ ሰው በዛሉ ጊዜ፥ ነፍሳቸውም በእናቶቻቸው ብብት በወጣች ጊዜ፥ እናቶቻቸውን። እህልና የወይን ጠጅ ወዴት አለ? ይሉአቸዋል። |
| 13. | ሜም። የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፥ ምን እመሰክርልሻለሁ? በምንስ እመስልሻለሁ? ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ አጽናናሽ ዘንድ በምን አስተካክልሻለሁ? ስብራትሽ እንደ ባሕር ታላቅ ነውና፤ የሚፈውስሽ ማን ነው? |
| 14. | ኖን። ነቢያቶችሽ ከንቱና ሐሰተኛ ራእይ አይተውልሻል፤ ምርኮሽንም ይመልሱ ዘንድ በደልሽን አልገለጡም፤ ከንቱና የማይረባ ነገርንም አይተውልሻል። |
| 15. | ሳምኬት። መንገድ አላፊዎች ሁሉ እጃቸውን ያጨበጭቡብሻልና። በውኑ የውበት ፍጻሜና የምድር ሁሉ ደስታ የሚሉአት ከተማ ይህች ናትን? እያሉ፥ በኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ላይ ያፍዋጫሉ፥ ራሳቸውንም ያነቃንቃሉ። |
| 16. | ዔ። ጠላቶችሽ ሁሉ አፋቸውን አላቀቁብሽ፤ እያፍዋጩና ጥርሳቸውን እያፋጩ። ውጠናታል፤ ነገር ግን ተስፋ ያደረግናት ቀን ይህች ናት፤ አግኝተናታል አይተናትማል ይላሉ። |
| 17. | ፌ። እግዚአብሔር ያሰበውን አደረገ፤ በቀድሞ ዘመን ያዘዘውን ቃል ፈጸመ፤ አፈረሰ አልራራምም፤ ጠላትንም ደስ አሰኘብሽ፥ የሚያስጨንቁሽንም ቀንድ ከፍ ከፍ አደረገ። |
| 18. | ጻዴ። ልባቸው ወደ ጌታ ጮኸ። የጽዮን ሴት ልጅ ቅጥር ሆይ፥ እንባሽን እንደ ፈሳሽ ቀንና ሌሊት አፍስሺ፤ ለሰውነትሽ ዕረፍት አትስጪ፤ የዓይንሽ ብሌን አታቋርጥ። |
| 19. | ቆፍ። ተነሺ፥ በሌሊት በመጀመሪያ ክፍል ጩኺ፥ በጌታም ፊት ልብሽን እንደ ውኃ አፍስሺ፤ በጐዳና ሁሉ ራስ ላይ በራብ ስለ ደከሙ ስለ ሕፃናትሽ ነፍስ እጆችሽን ወደ እርሱ አንሺ። |
| 20. | ሬስ። አቤቱ፥ እይ፤ በማን ላይ እንደዚህ እንዳደረግህ ተመልከት። በውኑ ሴቶች ፍሬያቸውን፥ ያቀማጠሉአቸውን ሕፃናት፥ ይበላሉን? በውኑ ካህኑና ነቢዩ በጌታ መቅደስ ውስጥ ይገደላሉን? |
| 21. | ሳን። ብላቴናውና ሽማግሌው በመንገዶች ላይ ተጋደሙ፤ ደናግሎቼና ጐበዛዝቴ በሰይፍ ወድቀዋል፤ በቍጣህ ቀን ገደልሃቸው፤ ሳትራራ አረድሃቸው። |
| 22. | ታው። እንደ በዓል ቀን የሚያስፈሩኝን ከዙሪያዬ ጠራህ፥ በእግዚአብሔር ቍጣ ቀንም ያመለጠ ወይም የቀረ አልተገኘም፤ ያቀማጠልኋቸውንና ያሳደግኋቸውን ጠላቴ በላቸው። |
| ← Lamentations (2/5) → |