Lamentations (1/5)  

1. አሌፍ። ሕዝብ ሞልቶባት የነበረች ከተማ ብቻዋን እንዴት ተቀመጠች! በአሕዛብ መካከል ታላቅ የነበረች እንደ መበለት ሆናለች፤ በአውራጆች መካከል ልዕልት የነበረች ተገዢ ሆናለች።
2. ቤት። በሌሊት እጅግ ታላቅሳለች፥ እንባዋም በጕንጭዋ ላይ አለ፤ ከውሽሞችዋ ሁሉ የሚያጽናናት የለም፤ ወዳጆችዋ ሁሉ ወነጀሉአት ጠላቶችም ሆኑአት።
3. ጋሜል። ይሁዳ ስለ መጨነቅና ስለ ባርነት ብዛት ተማረከች፤ በአሕዛብ መካከል ተቀመጠች ዕረፍትም አላገኘችም፤ የሚያስጨንቁአት ሁሉ ተጨንቃ አገኙአት።
4. ዳሌጥ። ወደ ዓመት በዓልም የሚመጣ የለምና የጽዮን መንገዶች አለቀሱ፤ በሮችዋ ሁሉ ፈርሰዋል ካህናቶችዋም እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ደናግሎችዋም ተጨነቁ እርስዋም በምሬት አለች።
5. ሄ። ስለ ኃጢአትዋ ብዛት እግዚአብሔር አስጨንቆአታልና አስጨናቂዎችዋ ራስ ሆኑ ጠላቶችዋም ተከናወነላቸው፤ ሕፃናቶችዋ በአስጨናቂዎች ፊት ተማርከዋል።
6. ዋው። ከጽዮን ሴት ልጅ ውበትዋ ሁሉ ወጥቶአል፤ አለቆችዋ ማሰማርያ እንደማያገኙ ዋላዎች ሆኑ፤ ከሚያባርሩአቸው ፊት ተዳክመው ሄዱ።
7. ዛይ። ኢየሩሳሌም በጭንቀትዋና በመከራዋ ወራት ከጥንት ጀምሮ የነበረላትን የከበረን ነገር ሁሉ አሰበች፤ ሕዝብዋ በአስጨናቂዎች እጅ በወደቀ ጊዜ የሚረዳትም በሌላት ጊዜ፥ አስጨናቂዎች አዩአት በመፍረስዋም ሳቁ።
8. ሔት። ኢየሩሳሌም እጅግ ኃጢአት ሠርታለች፤ ስለዚህ ረክሳለች፤ ያከብሩአት የነበሩ ሁሉ ኀፍረተ ሥጋዋን አይተዋታልና አቃለሉአት፤ እርስዋም እየጮኸች ታለቅሳለች ወደ ኋላም ዘወር አለች።
9. ጤት። አደፍዋ በልብስዋ ዘርፍ ነበረ፤ ፍጻሜዋን አላሰበችም፤ ስለዚህ በድንቅ ተዋርዳለች፥ የሚያጽናናትም የለም፤ አቤቱ፥ ጠላት ከፍ ከፍ ብሎአልና መከራዬን ተመልከት።
10. ዮድ። አስጨናቂው በከበረ ነገርዋ ሁሉ ላይ እጁን ዘረጋ፤ ወደ ጉባኤህ እንዳይገቡ ያዘዝሃቸው አሕዛብ ወደ መቅደስዋ ሲገቡ አይታለችና።
11. ካፍ። ሕዝብዋ ሁሉ እየጮኹ ያለቅሳሉ እንጀራም ይፈልጋሉ፤ ሰውነታቸውን ለማበርታት የከበረ ሀብታቸውን ስለ መብል ሰጥተዋል፤ አቤቱ፥ ተጐሳቍያለሁና እይ፥ ተመልከትም።
12. ላሜድ። እናንተ መንገድ አላፊዎች ሁሉ፥ በእናንተ ዘንድ ምንም የለምን? እግዚአብሔር በጽኑ ቍጣው ቀን እኔን እንዳስጨነቀበት በእኔ ላይ እንደ ተደረገው እንደ እኔ መከራ የሚመስል መከራ እንዳለ ተመልከቱ፥ እዩ።
13. ሜም። ከላይ እሳትን ወደ አጥንቴ ሰደደ በረታችበትም፤ ለእግሬ ወጥመድ ዘረጋ ወደ ኋላም መለሰኝ፥ አጠፋኝም ቀኑንም ሁሉ አደከመኝ።
14. ኖን። የኃጢአቶቼ ቀንበር በእጁ ተይዛለች፤ ታስረው በአንገቴ ላይ ወጥተዋል፤ ጕልበቴን አደከመ። ጌታ በፊታቸው እቆም ዘንድ በማልችላቸው እጅ አሳልፎ ሰጠኝ።
15. ሳምኬት። ጌታ ኃያላኖቼን ሁሉ ከውስጤ አስወገዳቸው፤ ጕልማሶቼን ያደቅቅ ዘንድ ጉባኤን ጠራብኝ፤ ጌታ ድንግሊቱን የይሁዳን ልጅ በመጥመቂያ እንደሚረገጥ አድርጎ ረገጣት።
16. ዔ። የሚያጽናናኝ ነፍሴንም የሚያበረታት ከእኔ ርቆአልና ስለዚህ አለቅሳለሁ፤ ዓይኔ፥ ዓይኔ ውኃ ያፈስሳል። ጠላት በርትቶአልና ልጆቼ ጠፍተዋል።
17. ፌ። ጽዮን እጅዋን ዘረጋች፤ የሚያጽናናት የለም፤ እግዚአብሔር በያዕቆብ ዙሪያ ያሉትን እንዲያስጨንቁት አዘዘ፤ ኢየሩሳሌም በመካከላቸው እንደ ርኩስ ነገር ሆናለች።
18. ጻዴ። በአፉ ነገር ላይ ዓመፅ አድርጌአለሁና እግዚአብሔር ጻድቅ ነው። እናንተ አሕዛብ ሁሉ፥ እባካችሁ፥ ስሙ መከራዬንም ተመልከቱ፤ ደናግሎቼና ጐበዛዝቴ ተማርከው ሄዱ።
19. ቆፍ። ውሽሞቼን ጠራሁ እነርሱም አታለሉኝ፤ ካህናቶቼና ሽማግሌዎቼ ሰውነታቸውን ያበረቱ ዘንድ መብል ሲፈልጉ በከተማ ውስጥ ሞቱ።
20. ሬስ። አቤቱ፥ ተጨንቄአለሁና፥ አንጀቴም ታውኮብኛልና ተመልከት፤ ዓመፃን ፈጽሞ አድርጌአለሁና ልቤ በውስጤ ተገላበጠብኝ፤ በሜዳ ሰይፍ ልጆቼን አጠፋ በቤትም ሞት አለ።
21. ሳን። እኔ እየጮኽሁ እንደማለቅስ ሰምተዋል፤ የሚያጽናናኝ የለም፤ ጠላቶቼ ሁሉ ስለ መከራዬ ሰምተዋል፤ አንተ አድርገኸዋልና ደስ አላቸው፤ ስለ እርሱ የተናገርኸውን ቀን ታመጣለህ እነርሱም እንደ እኔ ይሆናሉ።
22. ታው። ልቅሶዬ እጅግ ነውና፥ ልቤም ደክሞአልና ክፋታቸው ሁሉ ወደ ፊትህ ይድረስ፥ ስለ ኃጢአቴ ሁሉ እንዳደረግህብኝ አድርግባቸው።

      Lamentations (1/5)