| ← Judges (8/21) → |
| 1. | የኤፍሬም ሰዎች። ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ምድያምን ለመዋጋት በወጣህ ጊዜ ለምን አልጠራኸንም? አሉት። ጽኑ ጥልም ተጣሉት። |
| 2. | እርሱም። እኔ ካደረግሁት እናንተ ያደረጋችሁት አይበልጥምን? የኤፍሬም ወይን ቃርሚያ ከአቢዔዝር ወይን መከር አይሻልምን? |
| 3. | እግዚአብሔር የምድያምን መኳንንት ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል፤ እናንተ ያደረጋችሁትን የሚመስል እኔ ምን ማድረግ እችል ኖሮአል? አላቸው። ይህን በተናገረ ጊዜ ቍጣቸው በረደ። |
| 4. | ጌዴዎንም ከሦስቱ መቶ ሰዎች ጋር ወደ ዮርዳኖስ ደርሶ ተሻገረ፤ ምንም እንኳ ቢደክሙ ያሳድዱ ነበር። |
| 5. | የሱኮትንም ሰዎች። የምድያምን ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን ሳሳድድ፥ ደክመዋልና እኔን ለተከተሉ ሕዝብ እንጀራ፥ እባካችሁ፥ ስጡ አላቸው። |
| 6. | የሱኮትም አለቆች። እኛ ለሠራዊትህ እንጀራ እንድንሰጥ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን? አሉ። |
| 7. | ጌዴዎንም። እግዚአብሔር ዛብሄልንና ስልማናን በእጄ አሳልፎ ሲሰጠኝ እኔ በምድረ በዳ እሾህና በኵርንችት ሥጋችሁን እገርፋለሁ አለ። |
| 8. | ከዚያም ወደ ጵኒኤል ወጣ፥ ለጵኒኤልም ሰዎች እንዲሁ አላቸው፤ የጵንኤልም ሰዎች የሱኮት ሰዎች እንደ መለሱ መለሱለት። |
| 9. | እርሱም የጵኒኤልን ሰዎች ደግሞ። በደኅና በተመለስሁ ጊዜ ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ ብሎ ተናገራቸው። |
| 10. | ዛብሄልና ስልማናም ከሠራዊቶቻቸው ጋር በቀርቀር ነበሩ፤ ሰይፍ የሚመዝዙ መቶ ሀያ ሺህ ሰዎች ወድቀው ነበርና ከምሥራቅ ሰዎች ሠራዊት ሁሉ የቀሩ አሥራ አምስት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ። |
| 11. | ጌዴዎንም የድንኳን ተቀማጮች ባሉበት መንገድ በኖባህና በዮግብሃ በምሥራቅ በኩል ወጣ፤ ሠራዊቱም ተዘልሎ ነበርና ሠራዊቱን መታ። |
| 12. | ዛብሄልና ስልማናም ሸሹ፤ እርሱም አሳደዳቸው፥ ሁለቱንም የምድያም ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን ያዘ፥ ሠራዊቱንም ሁሉ አስደነገጠ። |
| 13. | የኢዮአስ ልጅም ጌዴዎን ከሔሬስ ዳገት ከሰልፍ ተመለሰ። |
| 14. | ከሱኮትም ሰዎች አንድ ብላቴና ይዞ ጠየቀው፤ እርሱም የሱኮትን አለቆችና ሽማግሌዎች ሰባ ሳባት ሰዎች ጻፈለት። |
| 15. | ወደ ሱኮትም ሰዎች መጥቶ። ለደከሙት ሰዎችህ እንጀራ እንሰጥ ዘንድ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን? ብላችሁ የተላገዳችሁብኝ፥ ዛብሄልና ስልማና እነሆ፥ አለ። |
| 16. | የከተማይቱንም ሽማግሌዎች ያዘ፥ የምድረ በዳንም እሾህና ኵርንችት ወስዶ የሱኮትን ሰዎች ገረፋቸው። |
| 17. | የጵኒኤልንም ግንብ አፈረሰ፥ የከተማይቱንም ሰዎች ገደላቸው። |
| 18. | ዛብሄልንና ስልማናን። በታቦር የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ? አላቸው። እነርሱም። እንደ አንተ ያሉ ነበሩ፥ አንተንም ይመስሉ ነበር፤ መልካቸውም እንደ ንጉሥ ልጆች መልክ ነበረ ብለው መለሱለት። |
| 19. | እርሱም። የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ነበሩ፤ አድናችኋቸው ቢሆን ኖሮ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ አልገድላችሁም ነበር አለ። |
| 20. | በኵሩንም ዬቴርን። ተነሥተህ ግደላቸው አለው፤ ብላቴናው ግን ገና ብላቴና ነበረና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም። |
| 21. | ዛብሄልና ስልማናም። የሰው ኃይሉ እንደ ሰውነቱ ነውና አንተ ተነሥተህ ውደቅብን አሉት። ጌዴዎንም ተነሥቶ ዛብሄልንና ስልማናን ገደለ፥ በግመሎቻቸውም አንገት የነበሩትን ሥሉሴዎች ማረከ። |
| 22. | የእስራኤልም ሰዎች ጌዴዎንን። ከምድያም እጅ አድነኸናልና አንተ ልጅህም የልጅ ልጅህም ደግሞ ግዙን አሉት። |
| 23. | ጌዴዎንም። እኔ አልገዛችሁም፥ ልጄም አይገዛችሁም፤ እግዚአብሔር ይገዛችኋል አላቸው። |
| 24. | እስማኤላውያንም ስለ ነበሩ የወርቅ ጕትቻ ነበራቸውና ጌዴዎን። ሁላችሁ ከምርኮአችሁ ጕትቻችሁን እንድትሰጡኝ እለምናችኋለሁ አላቸው። |
| 25. | እነርሱም። ፈቅደን እንሰጥሃለን ብለው መለሱለት። መጎናጸፊያም አነጠፉ፥ ሰውም ሁሉ የምርኮውን ጕትቻ በዚያ ላይ ጣለ። |
| 26. | የለመነውም የወርቅ ጕትቻ ሚዛኑ፥ ከአምባሩ፥ ከድሪውም፥ የምድያምም ነገሥታት ከለበሱት ከቀዩ ቀሚስ፥ በግመሎቻቸውም አንገት ከነበሩት ሥሉሴዎች ሌላ፥ ሺህ ሰባት መቶ ሰቅለ ወርቅ ነበረ። |
| 27. | ጌዴዎንም ኤፉድ አድርጎ አሠራው፥ በከተማውም በዖፍራ አኖረው፤ እስራኤልም ሁሉ ተከትሎት አመነዘረበት፤ ለጌዴዎንና ለቤቱም ወጥመድ ሆነ። |
| 28. | ምድያምም በእስራኤል ልጆች ተዋረደ፥ ራሳቸውንም ዳግመኛ አላነሡም፤ በጌዴዎንም ዕድሜ ምድሪቱ አርባ ዓመት ዐረፈች። |
| 29. | የኢዮአስም ልጅ ይሩበኣል ሄዶ በቤቱ ተቀመጠ። |
| 30. | ለጌዴዎንም ብዙ ሚስቶች ነበሩትና ከወገቡ የወጡ ሰባ ልጆች ነበሩት። |
| 31. | በሴኬምም የነበረችው ቁባቱ ወንድ ልጅ ወለደችለት፥ ስሙንም አቤሜሌክ ብሎ ጠራው። |
| 32. | የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን በመልካም ሽምግልና ሞተ፥ በአቢዔዝራውያንም ከተማ በዖፍራ በነበረችው በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ። |
| 33. | እንዲህም ሆነ፤ ጌዴዎን ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመለሱ፥ በኣሊምንም ተከትለው አመነዘሩ፤ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ። |
| 34. | የእስራኤልም ልጆች በዙሪያቸው ከነበሩት ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ ያዳናቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን አላሰቡትም፤ |
| 35. | እርሱም ለእስራኤል በጎ ነገርን ሁሉ እንዳደረገ መጠን፥ እነርሱ ለጌዴዎን ለይሩበኣል ቤት ወረታ አላደረጉም። |
| ← Judges (8/21) → |