| ← Judges (5/21) → |
| 1. | በዚያም ቀን ዲቦራና የአቢኒኤም ልጅ ባርቅ እንዲህ ብለው ተቀኙ። |
| 2. | በእስራኤል ውስጥ መሪዎች ስለ መሩ፥ ሕዝቡም ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ስለ ሰጡ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ። |
| 3. | ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፤ መኳንንት ሆይ፥ አድምጡ፤ እኔ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ። |
| 4. | አቤቱ፥ ከሴይር በወጣህ ጊዜ፥ ከኤዶምያስም ሜዳ በተራመድህ ጊዜ፥ ምድሪቱ ተናወጠች፥ ሰማያቱም አንጠበጠቡ፤ ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠበጠቡ። |
| 5. | ተራሮች ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ቀለጡ፥ ያም ሲና ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ። |
| 6. | በዓናት ልጅ በሰሜጋር ዘመን፥ በኢያዔል ዘመን መንገዶች ተቋረጡ፤ መንገደኞች በስርጥ መንገድ ይሄዱ ነበር። |
| 7. | አንቺ፥ ዲቦራ፥ እስክትነሽ ድረስ፥ ለእስራኤልም እናት ሆነሽ እስክትነሽ ድረስ፥ ኃያላን በእስራኤል ዘንድ አነሱ፥ አለቁም። |
| 8. | አዲሶች አማልክትን መረጡ፤ በዚያ ጊዜ ሰልፍ በበሮች ሆነ፤ በአርባ ሺህ በእስራኤል ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታየም። |
| 9. | ልቤ ወደ እስራኤል አለቆች ነው፥ በሕዝቡ መካከል ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ወደ ሰጡት፤ እግዚአብሔርን አመስግኑ። |
| 10. | በነጫጭ አህዮች ላይ የምትጫኑ፥ በወላንሳ ላይ የምትቀመጡ፥ በመንገድም የምትሄዱ፥ ተናገሩ። |
| 11. | በማጠጫው መካከል ካሉት ከቀስተኞች ጩኸት ርቀው፥ በዚያ የእግዚአብሔርን ጽድቅ፥ በእስራኤል ላይ የግዛቱን ጽድቅ ይጫወታሉ፤ ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ በሮች ወረዱ። |
| 12. | ንቂ፥ ንቂ፥ ዲቦራ ሆይ፤ ንቂ፥ ንቂ፥ ቅኔውን ተቀኚ፤ ባርቅ ሆይ፥ ተነሣ፤ የአቢኒኤም ልጅ ሆይ፥ ምርኮህን ማርክ። |
| 13. | በዚያ ጊዜ የቀሩት ወደ ኃያላኑና ወደ ሕዝቡ ወረዱ፤ እግዚአብሔርም ስለ እኔ በኃያላን ላይ ወረደ። |
| 14. | በአማሌቅ ዘንድ ሥር የነበራቸው እነርሱ ከኤፍሬም፥ ብንያም ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ከአንተ በኋላ ወረዱ፤ አለቆች ከማኪር፥ የንጉሥንም ዘንግ የሚይዙ ከዛብሎን ወረዱ። |
| 15. | የይሳኮርም አለቆች ከዲቦራ ጋር ነበሩ፤ ይሳኮርም እንደ ባርቅ ነበረ፤ ከእግሩ በኋላ ወደ ሸለቆው ቸኰሉ፤ በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ብዙ የልብ ማመንታት ነበረ። |
| 16. | መንጎች ሲያፍዋጩ ለመስማት በበጎች ጕረኖ መካከል ለምን ተቀመጥህ? በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ። |
| 17. | ገለዓድ በዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፤ ዳንም ለምን በመርከብ ውስጥ ቀረ? አሴርም በባሕሩ ዳር ተቀመጠ፥ በወንዞቹም ዳርቻ ዐረፈ። |
| 18. | ዛብሎን ነፍሱን ወደ ሞት ያሳለፈ ሕዝብ ነው፥ ንፍታሌምም በአገሩ ኮረብታ ላይ ነው። |
| 19. | ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፤ በዚያ ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፤ የብር ዘረፋም አልወሰዱም። |
| 20. | ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፤ በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ። |
| 21. | ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው። ነፍሴ ሆይ፥ በኃይል እርገጪ። |
| 22. | ከኃያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ። |
| 23. | የእግዚአብሔር መልአክ። ሜሮዝን እርገሙ፤ እግዚአብሔርን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥ እግዚአብሔርን ለመርዳት አልመጡምና የተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ። |
| 24. | የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፤ በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን። |
| 25. | ውኃ ለመነ፥ ወተትም ሰጠችው፤ በተከበረ ዳካ እርጎ አቀረበችለት። |
| 26. | እጅዋን ወደ ካስማ፥ ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፤ በመዶሻውም ሲሣራን መታች፥ ራሱንም ቸነከረች፤ ጆሮግንዱንም በሳች፥ ጎዳችውም። |
| 27. | በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ ተኛ፤ በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፤ በተደፋበት ስፍራ በዚያ ወድቆ ሞተ። |
| 28. | ከመስኮት ሆና ተመለከተች፤ የሲሣራ እናት በሰቅሰቅ ዘልቃ። ስለ ምን ለመምጣት ሰረገላው ዘገየ? ስለ ምንስ የሰረገላው መንኰራኵር ቈየ? ብላ ጮኸች። |
| 29. | ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፤ እርስዋ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች። |
| 30. | ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን? ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቈነጃጅት፤ ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፥ በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጕርጕር ልብስ። |
| 31. | አቤቱ፥ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፤ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፥ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች። |
| ← Judges (5/21) → |