← Judges (4/21) → |
1. | ናዖድም ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ። |
2. | እግዚአብሔርም በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቢስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ በአሕዛብ አሪሶት የተቀመጠው ሲሣራ ነበረ። |
3. | የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና፥ የእስራኤልንም ልጆች ሀያ ዓመት ያህል እጅግ ያስጨንቃቸው ነበር። |
4. | በዚያ ጊዜም ነቢይቱ የለፊዶት ሚስት ዲቦራ በእስራኤል ላይ ትፈርድ ነበረች። |
5. | እርስዋም በተራራማው በኤፍሬም አገር በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዛፍ ከሚባለው ከዘንባባው በታች ተቀምጣ ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እርስዋ ለፍርድ ይወጡ ነበር። |
6. | ልካም ከቃዴስ ንፍታሌም የአቢኒኤምን ልጅ ባርቅን ጠርታ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር። ሄደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ፥ ከአንተም ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን ልጆች አሥር ሺህ ሰዎች ውሰድ፤ |
7. | እኔም የኢያቢስን ሠራዊት አለቃ ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሕዝቡንም ሁሉ ወደ አንተ ወደ ቂሶን ወንዝ እስባለሁ፥ በእጅህም አሳልፌ እሰጠዋለሁ ብሎ አላዘዘህምን? አለችው። |
8. | ባርቅም። አንቺ ከእኔ ጋር ብትሄጂ እኔ እሄዳለሁ፤ አንቺ ግን ከእኔ ጋር ባትሄጂ እኔ አልሄድም አላት። |
9. | እርሷም። በእውነት ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሲሣራን በሴት እጅ አሳልፎ ይሰጣልና በዚህ በምትሄድበት መንገድ ለአንተ ክብር አይሆንም አለችው። ዲቦራም ተነሥታ ከባርቅ ጋር ወደ ቃዴስ ሄደች። |
10. | ባርቅም ዛብሎንንና ንፍታሌምን ወደ ቃዴስ ጠራቸው፥ አሥር ሺህም ሰዎች ተከትለውት ወጡ፤ ዲቦራም ከእርሱ ጋር ወጣች። |
11. | ቄናዊውም ሔቤር ከሙሴ አማት ከኦባብ ልጆች ከቄናውያን ተለይቶ ድንኳኑን በቃዴስ አጠገብ በጻዕናይም እስከ ነበረው እስከ ትልቁ ዛፍ ድረስ ተከለ። |
12. | የአቢኒኤምም ልጅ ባርቅ ወደ ታቦር ተራራ እንደ ወጣ ለሲሣራ ነገሩት። |
13. | ሲሣራም ሰረገሎቹን ሁሉ፥ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች፥ ከእርሱም ጋር የነበሩትን ሕዝቡን ሁሉ ከአሪሶት ወደ ቂሶን ወንዝ ሰበሰባቸው። |
14. | ዲቦራም ባርቅን። እግዚአብሔር ሲሣራን በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥበት ቀን ዛሬ ነውና ተነሣ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር በፊትህ ወጥቶአል አለችው። ባርቅም አሥር ሺህ ሰዎች ተከትለውት ከታቦር ተራራ ወረደ። |
15. | እግዚአብሔርም ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው፤ ሲሣራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ። |
16. | ባርቅም ሰረገሎችንና ሠራዊቱን እስከ አሪሶት ድረስ አባረረ፤ የሲሣራም ሠራዊት ሁሉ በሰይፍ ስለት ወደቀ፤ አንድ እንኳ አልቀረም። |
17. | በአሶር ንጉሥም በኢያቢስና በቄናዊው በሔቤር ቤት መካከል ሰላም ነበረና ሲሣራ በእግሩ ሸሽቶ ወደ ቄናዊው ወደ ሔቤር ሚስት ወደ ኢያዔል ድንኳን ደረሰ። |
18. | ኢያዔልም ሲሣራን ለመገናኘት ወጥታ። ግባ፥ ጌታዬ ሆይ፥ ወደ እኔ ግባ፤ አትፍራ አለችው። ወደ እርስዋም ወደ ድንኳንዋ ገባ፥ በመጐናጸፊያዋም ሸፈነችው። |
19. | እርሱም። ጠምቶኛልና እባክሽ የምጠጣው ጥቂት ውኃ ስጭኝ አላት፤ እርስዋም የወተቱን አቁማዳ ፈትታ አጠጣችው፥ ሸፈነችውም። |
20. | እርሱም። ከድንኳኑ ደጃፍ ቁሚ፤ ሰውም መጥቶ። በዚህ ሰው አለን? ብሎ ቢጠይቅሽ አንቺ። የለም ትዪዋለሽ አላት። |
21. | የሔቤርም ሚስት ኢያዔል የድንኳን ካስማ ወሰደች፥ በእጅዋም መዶሻ ያዘች፥ ቀስ ብላም ወደ እርሱ ቀረበች፤ በጆሮግንዱ ካስማውን ቸነከረች፤ እርሱም ደክሞ እንቀላፍቶ ነበርና ካስማው ወደ መሬት ጠለቀ፥ እርሱም ሞተ። |
22. | እነሆም፥ ባርቅ ሲሣራን ሲያባርር ኢያዔል ልትገናኘው ወጥታ። ና የምትሻውንም ሰው አሳይሃለሁ አለችው። ወደ እርስዋም ገባ፥ እነሆም፥ ሲሣራን ወድቆ ሞቶም አገኘው፥ ካስማውም ከጆሮግንዱ ውስጥ ነበረ። v |
23. | በዚያም ቀን እግዚአብሔር የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስን በእስራኤል ልጆች ፊት አዋረደ። |
24. | የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስንም እስኪያጠፉ ድረስ በከነዓን ንጉሥ በኢያቢስ ላይ የእስራኤል ልጆች እጅ እየበረታች ሄደች። |
← Judges (4/21) → |