Judges (3/21)  

2. ከከነዓናውያንም ጋር መዋጋት ያላወቁትን እስራኤልን በእነርሱ ይፈትናቸው ዘንድ፥ በፊትም ሰልፍን ያልለመዱ የእስራኤል ልጆች ትውልድ መዋጋትን ያውቁና ይማሩ ዘንድ እግዚአብሔር ያስቀራቸው አሕዛብ እነዚህ ናቸው፤
3. አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ ከነዓናውያንም ሁሉ፥ ሲዶናውያንም፥ ከበኣልአርሞንዔም ተራራ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ በሊባኖስ ተራራ የሚኖሩትም ኤዊያውያን።
4. እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ለአባቶቻቸው ያዘዘውን ትእዛዝ መስማታቸው እንዲታወቅ እስራኤል ይፈተኑባቸው ዘንድ እነዚህ ቀሩ።
5. የእስራኤልም ልጆች በከነዓናውያን በኬጢያውያንም በአሞራውያንም በፌርዛውያንም በኤዊያውያንም በኢያቡሳውያንም መካከል ተቀመጡ።
6. ሴት ልጆቻቸውንም አገቡአቸው፥ እነርሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻቸው ሰጡ፥ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ።
7. የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር አደረጉ፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረስተው በኣሊምንና አስታሮትን አመለኩ።
8. ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በመስጴጦምያ ንጉሥ በኵሰርሰቴም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የእስራኤልም ልጆች ለኵሰርሰቴም ስምንት ዓመት ተገዙለት።
9. የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም የሚያድናቸውን አዳኝ የካሌብን የታናሽ ወንድሙን የቄኔዝን ልጅ ጎቶንያልን አስነሣላቸው።
10. የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ መጣ፥ በእስራኤልም ላይ ይፈርድ ነበር፤ ለሰልፍ ወጣ፥ እግዚአብሔርም የመስጴጦምያን ንጉሥ ኵሰርሰቴምን በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እጁም በኵሰርሰቴም ላይ አሸነፈች።
11. ምድሪቱም አርባ ዓመት ዐረፈች፤ የቄኔዝም ልጅ ጎቶንያል ሞተ።
12. የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር የሞዓብን ንጉሥ ዔግሎምን በእስራኤል ላይ አበረታባቸው።
13. የአሞንን ልጆችና አማሌቅን ወደ እርሱ ሰበሰበ፤ ሄዶም እስራኤልን መታ፥ ዘንባባም ያለባትን ከተማ ያዙአት።
14. የእስራኤልም ልጆች ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎም አሥራ ስምንት ዓመት ተገዙለት።
15. የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም ብንያማዊውን የጌራን ልጅ ናዖድን ግራኙን ሰው አዳኝ አስነሣላቸው፤ የእስራኤልም ልጆች በእርሱ እጅ ወደ ሞዓብ ንጉሥ ወደ ዔግሎም ግብር ላኩ።
16. ናዖድም ሁለት አፍ ያለው ርዝመቱ አንድ ክንድ የሆነ ሰይፍ አበጀ፥ ከልብሱም በታች በቀኝ ጭኑ በኩል አደረገው።
17. ለሞዓብም ንጉሥ ለዔግሎም ግብሩን አቀረበ፤ ዔግሎምም እጅግ ወፍራም ሰው ነበረ።
18. ግብሩንም ማቅረብ በጨረሰ ጊዜ፥ ግብር የተሸከሙትን ሰዎች ሰደደ።
19. ናዖድ ግን በጌልገላ ከነበሩት ትክል ድንጋዮች ዘንድ ተመልሶ። ንጉሥ ሆይ፥ የምሥጢር ነገር አለኝ አለ፤ ንጉሡም። ዝም በል አለ፤ በዙሪያውም የቆሙት ሁሉ ወጡ።
20. ናዖድም ወደ እርሱ ቀረበ፤ እርሱም በሰገነት ቤት ለብቻው ተቀምጦ ነበር። ናዖድም። የእግዚአብሔር መልእክት ለአንተ አለኝ አለ። ከዙፋኑም ተነሣ።
21. ናዖድም ግራ እጁን ዘርግቶ ከቀኝ ጭኑ ሰይፉን ወሰደ፥ ሆዱንም ወጋው፤
22. የሰይፉም እጀታው ደግሞ ከስለቱ በኋላ ገባ፤ ስቡም ስለቱን ከደነው፥ ሰይፉንም ከሆዱ መልሶ አላወጣውም፤ በኋላውም ወጣ።
23. ናዖድም ወደ ደርቡ ወጣ፥ የሰገነቱንም ደጅ ዘግቶ ቈለፈው።
24. ናዖድም ከሄደ በኋላ ባሪያዎቹ መጡ፤ የሰገነቱም ደጅ ተቈልፎ ባዩ ጊዜ። ምናልባት በሰገነቱ ውስጥ ወገቡን ይሞክር ይሆናል አሉ።
25. እስኪያፍሩም ድረስ እጅግ ዘገዩ፤ የሰገነቱንም ደጅ እንዳልከፈተ ባዩ ጊዜ መክፈቻውን ወስደው ከፈቱ፥ እነሆም፥ ጌታቸው በምድር ወድቆ ሞቶም አገኙት።
26. በዘገዩበትም ጊዜያት ናዖድ ሸሸ፥ ትክል ድንጋዮቹንም አለፈ፥ ወደ ቤይሮታም አመለጠ።
27. በመጣም ጊዜ በተራራማው በኤፍሬም አገር ቀንደ መለከት ነፋ፤ የእስራኤልም ልጆች ከእርሱ ጋር ከተራራማው አገር ወረዱ፥ እርሱም በፊታቸው ሄደ።
28. እርሱም። እግዚአብሔር ጠላቶቻችሁን ሞዓባውያንን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተከተሉኝ አላቸው። ተከትለውትም ወረዱ፥ ወደ ሞዓብም የሚያሻግረውን የዮርዳኖስን መሻገርያ ያዙ፥ ማንንም አላሳለፉም።
29. የዚያን ጊዜም ከሞዓብ አሥር ሺህ የሚያህሉትን፥ ጕልማሶችና ጽኑዓን ሁሉ፥ መቱ፤ አንድ እንኳ አላመለጠም።
30. በዚያም ቀን ሞዓብ ከእስራኤል እጅ በታች ተዋረደ፤ ምድሪቱም ሰማንያ ዓመት ዐረፈች።
31. ከእርሱም በኋላ የዓናት ልጅ ሰሜጋር ተነሣ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ስድስት መቶ ሰው በበሬ መውጊያ ገደለ፤ እርሱም ደግሞ እስራኤልን አዳነ።

  Judges (3/21)