Judges (21/21)    

1. የእስራኤልም ሰዎች። ከእኛ ማንም ሰው ልጁን ለብንያም ልጆች አያጋባ ብለው በምጽጳ ተማምለው ነበር።
2. ሕዝቡም ወደ ቤቴል መጥተው በዚያ በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ድረስ ተቀመጡ፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጽኑ ልቅሶ አለቀሱ።
3. እነርሱም። አቤቱ፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ መታጣቱ፥ ስለ ምን ይህ በእስራኤል ላይ ሆነ? አሉ።
4. በነጋውም ሕዝቡ ማልደው ተነሡ፥ በዚያም መሠዊያ ሠሩ፥ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕትንም አቀረቡ።
5. የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ስላልወጣ ሰው። እርሱ ፈጽሞ ይገደል ብለው ታላቅ መሐላ ምለው ነበርና። ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ወደ ጉባኤ ወደ እግዚአብሔር ያልወጣ ማን ነው? አሉ።
6. የእስራኤልም ልጆች ስለ ወንድሞቻቸው ስለ ብንያም ልጆች ተጸጽተው። ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ ጠፍቶአል።
7. እኛ ልጆቻችንን እንዳንድርላቸው በእግዚአብሔር ምለናልና የተረፉት ሚስቶችን እንዲያገኙ ምን እናድርግ? አሉ።
8. እነርሱም። ከእስራኤል ነገድ ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ያልወጣ ማን ነው? አሉ። እነሆም፥ ከኢያቢስ ገለዓድ ወደ ሰፈሩ ወደ ጉባኤ ማንም አልወጣም ነበር።
9. ሕዝቡም በተቈጠሩ ጊዜ፥ እነሆ፥ በኢያቢስ ገለዓድ የሚኖር ሰው አልተገኘም።
10. ማኅበሩም ወደዚያ አሥራ ሁለት ሺህ ኃያላን ሰዎች ሰድደው። ሂዱ በኢያቢስ ገለዓድም ያሉትን ሰዎች ከሴቶችና ከሕፃናት ጋር በሰይፍ ስለት ግደሉ።
11. የምታደርጉትም ይህ ነው፤ ወንዱን ሁሉ፥ ከወንድ ጋር የተኛችይቱንም ሴት ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ ብለው አዘዙአቸው።
12. ወንድ ያላወቁ አራት መቶ ቈነጃጅት ደናግሎች በኢያቢስ ገለዓድ በሚኖሩ መካከል አገኙ፤ በከነዓንም አገር ወዳለችው ወደ ሴሎ ወደ ሰፈሩ አመጡአቸው።
13. ማኅበሩም ሁሉ በሬሞን ዓለት ወዳሉት ወደ ብንያም ልጆች መልክተኞችን ላኩ፥ በዕርቅ ቃልም ተናገሩአቸው።
14. በዚያም ጊዜ የብንያም ልጆች ተመለሱ፤ ከኢያቢስ ገለዓድም ሴቶች ያዳኑአቸውን ሴቶች አገቡአቸው። ነገር ግን የሚበቁ ሴቶች አላገኙም።
15. እግዚአብሔርም በእስራኤል ነገድ ውስጥ ስብራት ስላደረገ ሕዝቡ ስለ ብንያም ተጸጸቱ።
16. የማኅበሩ ሽማግሌዎች። ከብንያም ሴቶች ጠፍተዋልና የቀሩት ሰዎች ሚስት እንዲያገኙ ምን እናደርጋለን? አሉ።
17. ደግሞም። ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዳይደመሰስ ከብንያም ላመለጡት ርስት ይኑር።
18. የእስራኤልም ልጆች። ልጁን ለብንያም የሚድር ርጉም ይሁን ብለው ምለዋልና እኛ ልጆቻችንን ለእነርሱ ማጋባት አይሆንልንም አሉ።
19. እነርሱም። እነሆ፥ በቤቴል በሰሜን በኩል፥ ከቤቴልም ወደ ሴኬም በሚወስደው መንገድ በምሥራቅ በኩል፥ በለቦና በደቡብ በኩል ባለችው በሴሎ የእግዚአብሔር በዓል በየዓመቱ አለ አሉ።
20. የብንያምንም ልጆች እንዲህ ብለው አዘዙአቸው። ሂዱ በወይኑ ስፍራ ተደበቁ፤
21. ተመልከቱም፥ እነሆም፥ የሴሎ ሴቶች ልጆች አታሞ ይዘው ለዘፈን ሲወጡ ከወይኑ ስፍራ ውጡ፥ ከሴሎም ሴቶች ልጆች ለየራሳችሁ ሚስት ንጠቁ፥ ወደ ብንያም ምድርም ሂዱ።
22. አባቶቻቸውና ወንድሞቻቸውም ሊጣሉአችሁ ወደ እኛ በመጡ ጊዜ። ስለ እኛ ማሩአቸው፤ እኛ ሚስት ለያንዳንዳቸው በሰልፍ አልወሰድንላቸውምና፥ እናንተም በደል ይሆንባችሁ ስለ ነበረ አላጋባችኋቸውምና፥ እንላችኋለን።
23. የብንያምም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ በቍጥራቸውም መጠን ከተነጠቁት ዘፋኞች ሚስት ወሰዱ፤ ወደ ርስታቸውም ተመልሰው ሄዱ፥ ከተሞችንም ሠርተው ተቀመጡባቸው።
24. በዚያን ጊዜም የእስራኤል ልጆች ከዚያ ተነሡ፥ እያንዳንዱም ወደ ነገዱና ወደ ወገኑ ሄደ፤ ሰውም ሁሉ ከዚያ ወደ ርስቱ ተመለሰ።
25. በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።

  Judges (21/21)